በአማራ ክልል ባሳለፍነው ሀምሌ ወር ብቻ ከ180 ሺ በላይ ሰዎች በወባ በሽታ ተይዘዋል ተባለ።

ከሀምሌ ወር ጀምሮ በየሳምንቱ ከ40 ሺ በላይ ሰዎች በወባ በሽታ መያዛቸውን የአማራ ክልል ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታውቋል።

በኢንስቲትዩት መስሪያ ቤቱ የወባ ኘሮግራም አስተባባሪ አቶ ዳምጤ ላንክር ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንደተናገሩት፣ ካለፈው አመት ጋር ሲነፃፀር 31 በመቶ ጭማሪ ያሳያል ብለዋል።

የወባ ስርጭቱ አሁን ካለበት በላይ አስከፊ ይሆናል ተብሎ የሚታሰበው በመስከረም እና በጥቅምት ወር መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ስርጭቱ አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ያነሱት አስተባባሪው፣ ባሁኑ ሰአት መቀነስ ካልቻለም የወባ ዋና መተላለፊያ በሚባሉት መስከረም እና ጥቅምት ወር ላይ ከባድ የሆነ ችግር ሊያስከትል እንደሚችል ገልፀዋል።

ችግሩን በተገቢው መንገድ ለመቅረፍ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በጋራ በመሆን ስራዎችን እየሰሩ እንደሚገኙም ተናግረዋል።
እንዲሁም ጫና ባለባቸው 22 ወረዳዎች እርጭት እየተከናወነ እንደሚገኝ አንስተዋል።

ማህበረሰቡም በወባ መከላከል እና መቆጣጠር ተግባር ላይ ተሳታፊ መሆን እንዳለበት እና፣ ወባን በማከም ብቻ መቆጣጠር ስለማይቻል፣ ወባን ለመከላከል ሁሉም የበኩሉን አስተዋፅኦ ማድረግ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
የተሰጠውን የመኝታ አጎበር በአግባቡ መጠቀምም አስፈላጊ ነው ሲሉ አሳስበዋል።

በሐመረ ፍሬው

ነሐሴ 06 ቀን 2016 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *