በባለፈዉ አመት ከነበረዉ የኤችአይቪ ኤድስ ተጠቂ ቁጥር ከ3.69 ወደ 3.2 በመቶ ዝቅ እንዲል ማድረግ መቻሉን የጋምቤላ ክልል ኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ኡኬሎ ቾል ለጣቢያችን ገልፀዋል።
ሀላፊዉ እንደገለፁት ስርጭቱ ከባለፈዉ አመት ጋር ሲነፃፀር ቅናሽ ቢያሳይም በህመሙ አብላጫዉን የሴት ተጠቂዎች ቁጥር እንደሚይዝ ታዉቋል።
በጋምቤላ ክልል ለኤችአይቪ ስርጭት አጋላጭ ናቸዉ ተብለዉ በተለዩ ቦታዎች አንዱ የሆነዉ የወርቅ ማዉጫ ስፍራዎች በቂ የኮንዶም ስርጭት እንዲኖር እየተደረገ መሆኑን ሀላፊዉ ተናግረዋል።

በክልሉ ነዋሪዎች የደም ምርመራ እያደረጉ መሆኑን እንዲሁም የኤችአይቪ ኤድስ መቆጣጠሪያ መድሀኒት አቅርቦት እጥረት እንዳይኖር እየተሰራ ነዉ ተብሏል።
የበሽታዉ ስርጭት ከፍተኛ እንደሆነባቸዉ ከሚነገርባቸዉ ክልሎች አንዱ የሆነዉ ጋምቤላ ክልል አንዳንድ ቦታዎች ላይ ከቱሪስት ፍሰቱ ጋር ተያይዞ ስለ በሽታዉ እዉቀት የሌላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች የመረጃ ተደራሽነት ክፍተቶች እንዳሉ ሀላፊዉ አያይዘዉ ተናግረዋል።
በተጠናቀቀው በጀት አመት በተለያዩ ወረዳዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን እየሰሩ እንደቆዩ የተናገሩት ሀላፊዉ 130 ሺህ ያህል ሰዎችን ማሰልጠን መቻላቸዉን ገልፀዋል።
የኢትዮጲያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዮት ባጠናው የቅርብ ጊዜ ጥናት አዲሰ አበባ ከተማ በኤችአይቪ ኤድስ ስርጭት የመጀመሪያ ደረጃ መያዟን አመላክቷል
በቁምነገር አየለ
ነሐሴ 08 ቀን 2016 ዓ.ም
