‘ጥቁር አደይ’ ፈልም በቴሌቲቪ መተግበሪያ ለዕይታ ሊቀርብ ነው ተባለ።

በአለም አቀፍ የፊልም መስፈርት የተሰራው ጥቁር አደይ ፊልም በቴሌቲቪ መተግበሪያ ከነሃሴ 22 / 2016 ዓ.ም መታየት እንደሚጀምር የፊልሙ አዘጋጆች አስታውቀዋል።

ጥቁር አደይ የተሰኘውን ፊልም የሃገር ዉስጥ የተመልካች ፍላጎትን በመመልከት ለሃገር ዉስጥ ተመልካቾች በቴሌቲቪ በኩል መቅረቡ ተነግሯል።

ለዚህ ፍላጎትም ቴሌቲቪ አስተማማኝ እና ተስማሚ ሆና ስላገኙት ፊልማቸዉን በቴሌቲቪ ለማሳየት መወሰናቸዉን አዘጋጆቹ ገልጸዋል።

ይሄ ፊልም ምንም እንኳን ኔትፍሊክስ ላይ እንዲታይ ታስቦ ቢሰራም ኤግልላይን ባቀረበው ተመጣጣኝ ድርድር ለሀገር ውስጥ ተመልካቾች ተመራጭ እና ልዩ በሆነው ቴሌቲቪ በኩል ሊቀርብ መቻሉን ሰምተናል።

በፊልሙ ላይ ከተሳተፉ ተዋንያኖች መካከል ናታይ ጌታቸው፣ካሳሁን ፍሰሃ ማንዴላ ፣ ነብዩ እንድሪስ እና ሌሎች ድንቅ የሃገራችን ተዋንያን የተካተቱበት ነው ተብሏል።

ዶቃ ፊልም ነሃሴ 11 ቀን 2016 ዓ.ም ቴሌቲቪ ላይ በይፋ መታየት መጀመሩ የሚታወስ ሲሆን አሁን ደግሞ ጥቁር አደይ የተሰኘው ፊልም ቴሌቲቪ ላይ መግባቱ ተገልጿል ።

ቴሌቲቪ ለገበያው አዲስ እና በአይነቱ የመጀመሪያ ቢሆንም በተመልካቾች ዘንድ መልካም አቀባበል እንዳለው የኢግልላይን መስራች እና ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ በእርሱፈቃድ ጌታቸው ገልጸዋል።

ቴሌቲቪ የፊልም ኢንደስትሪውን ለማሳደግ ትልቅ ሚና እንደሚኖረው የገለጹት አቶ በእርሱ ፈቃድ እንደ ጥቁር አደይ ያሉ ፊልሞች ወደ ቴሌቲቪ መግባታቸው ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖራቸዋል ብለዋል።

ቴሌቲቪ ከሃገር ዉስጥ ተመልካቾች አልፎ ለአለማቀፍ ገበያ የኢትዮጵያ ፊልሞችን ለማቅረብ እየሰራ እንደሚገኝ እና ለዚህም አለማቀፍ የክፍያ አማራጮች ማለትም ቪዛ፣ማስተርካርድ እና አሜሪካን ኤክስፕረስን በመጠቀም የቴሌቲቪ ፊልሞችን መከራየት እንደሚቻል ተገልጿል።

ተመልካቾች በቴሌቲቪ ካሉበት ቦታ ሆነው ኢንተርኔትን በመጠቀም ብቻ መተግበሪያው ላይ የተመረጡ ፊልሞችን ከየትኛውም ቦታ መመልከት እንደሚቻል ተገልጿል።

በሐመረ ፍሬዉ
ነሐሴ 17 ቀን 2016 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *