ዘመን ባንክ የኢትዮጵያ ኔዘርላንድ ቢዝነስ ማህበር አባል በመሆን አብሮ ለመስራት የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራርመዋል።
የኢትዮጵያ ኔዘርላንድ ቢዝነስ ማህበር(ENLBA) በኢትዮጵያ የኔዘርላንድ ኤምባሲ ስር የተቋቋመ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ ዘርፎች እየሰሩ ላሉ 60 ለሚሆኑ አባል ኩባንያዎች እንዳሉት ተገልጿል።
ማህበሩ ለአባላቶቹ አስፈላጊ የሆኑ የሀብት ማሰባሰብ፣ ማማከር እና መሰል ድጋፎችን በማድረግ አባላቱ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖራቸውን የአጋርነት ሚና ከፍ በማድረግ የንግድ እና ኢንቨስትመንት አቅምን ለማሳለጥ ስለመቋቋሙ ተሰምቷል።
በማህበሩ ስር ካሉ ዘርፈ ብዙ ኢንደስትሪዎች ጋር የሚኖረውን አጋርነትን ለማጠንከር እንዲሁም ዘላቂ የባንክ እገዛ እና አጋርነትን ከሚፈልጉ መሰል ተቋማት ጋር አብሮ የመስራት እቅዱን ለማሳካት የሚያስችል ስምምነት በባንኩ ዋና መስሪያ ቤት ተፈራርመዋል።
ዘመን ባንክ ከሀገር ውስጥ እና ከአለም አቀፍ ኩባንያዎች ጋር ዘላቂና ጠንካራ አጋርነት የሚገነባ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን፤ በዚህም ባንኩ ከኔዘርላንድ አበባ እና ፍራፍሬ ግብርና ማኖፋክቸሪንግ ኩባንያዎች ጋር ሲሰራ መቆየቱ በመግለጫው ተመላክቷል።
በመሆኑም የተከናወነው ስምምነቱ መሰል አጋርነትን ለማጠንከር፤ ለወደፊቱ ስልታዊ ጥምረት በመፍጠር ዘላቂ አጋርነት እንዲመሰረት እንደሚያስችል ተገልጿል።
ዘመን ባንክ በዋና መስሪያ ቤትና በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ ከ126 በላይ የቅርንጫፍ ቢሮዎች እንዳሉት ተመልክቷል።
በእሌኒ ግዛቸው
ነሐሴ 17 ቀን 2016 ዓ.ም
