ከተከሰሱት መሪዎች መሃከል አዲሱ የሃማስ መሪ ያህያ ሲንዋር ይገኝበታል፡፡
አሜሪካ ያህያ ሲንዋርን ጨምሮ በሃማስ ዉስጥ ቁልፍ ቦታ አላቸዉ የሚባሉ ግለሰቦችን ጥቅምት 7 እስራኤል ላይ ከደረሰዉ ጥቃት ጋር በተያያዘ በወንጀል መክሰሷን አስታዉቃለች፡፡
የፍትህ ዲፓርትመንቱ እንደገለጸዉ ፤ 6 ግለሰቦች በሰባት ክሶች የተከሰሱ ሲሆን፤ የአሜሪካ ዜጎችን በመግደል፣ በፋይናንስ ሽብር እንዲሁም ከፍተኛ አጥፊ መሳሪያዎችን መጠቀም የሚል ይገኝበታል፡፡
የወንጀል ክሱ ከ10 ዓመታት በላይ የቆየዉን የሃማስን ጥቃት እንዲሁም በጥቅምት 7 በደቡባዊ እስራኤል ያደረሰዉን ጥቃት የሚያጠቃለል ነዉ ፡፡
የአሜሪካ የህግ አስከባሪ በጥቅምት 7ቱ ጥቃት የተሳተፉ የሃማስ መሪዎችን ተጠያቂ የሚያደርግበት የመጀመሪያዉ ደረጃ መሆኑን የገለጸ ሲሆን፤ በጥብቅ ከሚፈለጉ ሶስት ግለሰቦች መካከል ሁለቱ በህይወት የሌሉ ሲሆን ያህያ ሲንዋር ደግሞ በጋዛ ዋሻዎች ዉስጥ ተደብቋል፡፡
ሃማስ በእድሜ የገፉ ሰዎችን ጨምሮ ህጻናትን ገድሏል፤ መድፈርን ጨምሮ በሴቶች ላይ ጾታዊ ጥቃትን አድርሷል የሚል ክስም በተጨማሪነት ቀርቦበታል፡፡
በወንጀል ከተከሰሱት የሃማስ መሪዎች መካከል የቀድሞዉ መሪ ኢስማኤል ሃኒዬህ፣ የቡድኑ ምክትል መሪ ማርዋን ኢሳ፣ ከዌስት ባንክ እና ጋዛ ዉጪ ቡድኑን የሚመራዉ ካሊድ ማሻልን ጨምሮ ሞሀመድ ዲይፍ እና አሊ ባራካ ይገኙበታል፡፡
ኢስማኤል ሃኒዬህ ፣ማርዋን ኢሳ እና ሞሃመድ ዲይፍ ባለፉት ወራት እስራኤል አድርሼዋለሁ ባለችዉ አልያም ድጋፍ አድርጋለች በተባለ ጥቃት ህይወታቸዉ አልፏል፡፡
እስከዳር ግርማ
ነሐሴ 29 ቀን 2016 ዓ.ም
