በተደረገ የቁጥጥር ስራ የዋጋ ዝርዝር ሳይለጥፉ የተገኙ እና ከግራም በታች ሲሸጡ የተገኙ 265 ዳቦ ቤቶች እርምጃ እንደተወሰደባቸው የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ አስታውቋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የንግድ ቢሮ የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሰውነት አየለ ለጣቢያችን እንደተናገሩት ዝቅተኛው የዳቦ ግራም 70 ግራም ነው ብለዋል።
ከተወሰደባቸው እርምጃዎች መካከል የማሸግ እና የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ ተጠቃሽ መሆናቸውን አንስተዋል ።
የከተማ አስተዳደሩ እና የግል ባለሀብቶች የገነቧቸው የገበያ ማእከላት ውስጥ የሚገኙ 17 የሚሆኑ ዳቦ ቤቶች አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ እና በከተማዋ ከ1 ሺ 3 መቶ በላይ የዳቦ ነጋዴዎች መኖራቸውንም ተናግረዋል፡፡
ማህበረሰቡም የትኛውም አካባቢ ላይ ከግራም በታች የሚሸጡ የዳቦ ነጋዴዎችን በሚያስተውልበት ወቅት 8588 ነፃ የስልክ መስመር ላይ በመደወል ጥቆማዎችን እንዲሰጡ የሚል መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል ።
ሐመረ ፍሬው
ጳጉሜ 1 ቀን 2016 ዓ.ም
