የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር በመሆን ለሚያከናውናቸው የመልሶ ግንባታና የአቅም ማሻሻያ ሥራዎች የሚውል 545 ሚሊዮን ዶላር ብድር ከዓለም ባንክ መገኘቱን አስታውቋል፡፡
የአገልግሎቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሽፈራው ተሊላ ፣ በ72 ከተሞች ቀደም ሲል የተጀመሩ የመልሶ ግንባታና የአቅም ማሻሻያ ሥራዎችን ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር ለመሥራት የሚያስችል የ545 ሚሊዮን ዶላር ብድር ከዓለም ባንክ መገኘቱን ገልጸዋል፡፡
በዚህም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል፣ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮችንና የአቅም ውስንነት ያለባቸውን የማከፋፈያ ጣቢያዎችን፣ እንዲሁም አገልግሎቱ በከተሞች ውስጥ ያለውን መሠረተ ልማት እንደሚገነባ አስታውቀው፣ የተገኘው ብድር ሁለቱ ተቋማት ለሚያከናውኑት ሥራ የሚውል መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ለዚህ ፕሮጀክት የሚውል የግዥና የኮንትራክተሮች መረጣም በተያዘው የ2017 በጀት ዓመት እንደሚከናወን ገልጸዋል፡፡
የኤሌክትሪክ ኃይል ፍጆታ ታሪፍ ማሻሻያውን በተመለከተ ማብራሪያ የሰጡት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ከመስከረም 1 ቀን 2017 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረግ ገልጸው፣ ተቋሙ ተጨማሪ ኢንቨስትመንት የመሥራት አቅም አንዲኖረው ለማስቻልና የኅብረተሰቡን የመክፈል አቅም ከግንዛቤ ማስገባት የሚሉ ሁለት ዋና ዋና ጉዳዮችን መሠረት አድርጎ የተደረገ ማሻሻያ መሆኑን አስታውቀዋል።
ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን
ጳጉሜ 4 ቀን 2016 ዓ.ም
