ተቋሙ በ2016 በጀት ዓመት ከ10 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠሩን ገለጸ፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በመላ ሀገሪቱ እያከናወናቸው በሚገኙ የኃይል ማመንጫ፣ ማስተላለፊያ መስመር፣ ማከፋፈያ ጣቢያ እና በሌሎች ፕሮጀክቶች 10 ሺህ 548 ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠሩን በተቋሙ የኮርፖሬት ፕላኒንግ ዘርፍ አስታውቋል፡፡

የዘርፉ ሥራ አስፈጻሚ አቶ አንዱአለም ሲዓ እንዳስታወቁት ተቋሙ የኃይል መሰረተ ልማት ፕሮጀክቶችን ለማስፋፋት እያከናወነ ካለው ሥራ ጎን ለጎን ለዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡

ተቋሙ የኃይል መሰረት ልማትን ከማስፋፋት በተጨማሪ በሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ የገለጹት ሥራ አስፈጻሚው በተጠናቀቀው በጀት ዓመትም ለ13 ሺህ 197 ዜጎች የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠር ታቅዶ ሲሰራ ነበር ብለዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ በመላ ሀገሪቱ ሲከናወኑ በነበሩ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ለ1 ሺህ 710 ሰዎች በቋሚነት፣ለ 8 ሺህ 389 ሰዎች በጊዜያዊነት እንዲሁም ለ 449 ሰዎች በኮንትራት የሥራ ዕድል ሲፈጠር ከእነዚህ መካከል 1 ሺህ አርባ የሚሆኑት ሴቶች መሆናቸውንም አቶ አንዱአለም ጠቅሰዋል፡፡

ይህም ተቋሙ በሀገሪቱ ያለውን የሥራ አጥ ቁጥር በመቀነስ በኩል የራሱን አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ያሳያል ብለዋል፡፡

ተቋሙ በበጀት ዓመቱ ለማከናወን ያቀዳቸውን ሥራዎችን በአግባቡ ለመፈጸም የፋይናንስ እጥረትና የጸጥታ ችግሮች እንቅፋት እንደነበሩ የተናገሩት አቶ አንዱአለም ይህም በሥራ ዕድል ፈጠራው ላይ የራሱ የሆነ ተፅዕኖ ስለማሳደሩ ተናግረዋል፡፡

በተያዘው የበጀት ዓመት ይጀመራሉ ተብለው የታቀዱ አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ጨምሮ በግንባታ ላይ ባሉት ነባር ፕሮጀክቶች 15 ሺህ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር መታቀዱንም ሥራ አስፈጻሚው ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን

ጳጉሜ 05 ቀን 2016 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *