በ2017 በጀት ዓመት ለሚያደርጋቸው የአገልግሎት ማስፋፊያዎች ከ1 ቢሊየን ዶላር በላይ በጀት መያዙን የኩባንያው ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ ገልጸዋል።
ኩባንያው በተያዘው በጀት አመት ከ1መቶ63 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ለማግኘት በዕቅድ መያዙንም ነው ዋና ስራ አስፈፃሚዋ የገለፁት።
ባለፈው ዓመት ከተገኘው የ93.7 ቢሊየን ብር ገቢ ላይ የ70 ቢሊየን ብር ጭማሪ በማድረግ ነው በዚህ አመት ከ1መቶ63 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ለማግኘት የታቀደው።
ኩባንያው ባለፈው ዓመት ካገኘው የ1መቶ98 ሚሊየን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ፤ የ84.8 ሚሊየን ዶላር ጭማሪ በማድረግ 2መቶ82 ሚሊየን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት መታቀዱንም ዋና ስራ አስፈፃሚዋ ገልጸዋል።
2016 በጀት አመት ሲጠናቀቅ የደንበኞች ቁጥር 78 ሚሊየን እንደነበር ያነሱት ወ/ት ፍሬህይወት ፤ በዚህ በጀት ዓመት መጠናቀቂያ ላይ 83 ሚሊየን ለመድረስ ታቅዷል ብለዋል።
የቴሌብር ደንበኞች ቁጥርን ደግሞ ባለፈው ዓመት ከነበረው 47.5 ሚሊየን ፤ 15.7 በመቶ ጭማሪ በማድረግ 55 ሚሊየን ለማድረስ በዕቅድ መያዙንም አንስተዋል።
በዚህ ዓመት 2መቶ60 አዳዲስ አገልግሎቶችን ለደንበኞቹ እንደሚያቀርብም ገልጸዋል።
በ2015 በጀት አመት ይፋ ያደረገው “መሪ” የተሰኘው የሶስት ዓመት የዕድገት ስትራቴጂ በዚህ አመት የሚጠናቀቅ መሆኑንም ዋና ስራ አስፈፃሚዋ አስታውቀዋል።
በእስከዳር ግርማ
መስከረም 9 ቀን 2017 ዓ.ም
