ምርጫ ቦርድ ያደረገው የክፍያ መሻሻያ የተጋነነ ነው ሲል የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርታዎች የጋራ ምክር ቤት ተቸ

የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ  ይፋ ያደረገው የአገልግሎት ክፍያ ጭማሪ ተገቢነት የሌለው  እና  የተጋነነ ነዉ ሲሉ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት  ሰብሳቢ አቶ ደስታ ዲንቃ  ለኢትዮ ኤፍ ኤም ተናግረዋል፡፡

ሰብሳቢው  ከጣቢያችን ጋር በነበራቸው ቆይታም ፤ቦርዱ ያደረገው  የአገልግሎት ክፍያ ጭማሪ ሁሉንም ፓርቲ ያላማከለ እና ቀደሞውኑ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ምክክር ያልተደረገበት እንደሆነ ለጣቢያችን ገልጸዋል፡፡

ሰብሳቢው አያይዘውም የዚህ ክፍያ ማሻሻያ  አቅም የሌላቸውን የፖለቲካ ፓርቲዎችን ያላገናዘበ እና የፖለቲካ ምህዳሩ ላይም የእራሱን ጠባሳ የሚያሳርፍ ነዉ ብለዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም ወደፊት በፓርቲ ደረጃ ለመቋቋም ያሰቡ ህዝቦቸን መብት በተወሰነ መልኩ ሊገድብ እንደሚችል ገለጸው፤ይህ ማለት የመደራጀት መብትን በተወሰነ መልኩ የሚገድብ እንደሆነም ነግረውናል፡፡

የፖለቲካ ምህዳሩ አሁንም ሰፋ ያለ አለመሆኑን የነገሩን ዋና ሰብሳቢው ፤ ይህ ማሻሻያ ደግሞ ከዚህ በላይ የፖለቲካ ምህዳሩን እንዳያጠበው ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ  ለፖለቲካ ፓርቲዎች በሚሰጣቸው ሶስት አገልግሎቶች ላይ ከጥቅምት 11፤ 2017 ጀምሮ ጭማሪ ማድረጉን ማስታወቁ ይታወቃል፡፡

በአዲሱ “የክፍያ ማሻሻያ ተመን መሰረት” ለጊዜያዊ እውቅና 15ሺ ብር፣ ለሙሉ እውቅና 30ሺ ብር፣ ለሰነድ ማሻሻያ ደግሞ 5ሺ ብር እንደሚያስከፍል ቦርዱ መግለጹ ይታወሳል፡፡

ለዓለም አሰፋ

ጥቅምት 14 ቀን 2017 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *