በደቡባዊ ቻይና በተፈጸመ የመኪና ጥቃት ቢያንስ 35 ሰዎች ተገደሉ። በአገሪቱ ባለፉት አሥርት ዓመታት በላይ በሕዝብ ላይ የተፈጸመ እጅግ አስከፊው ጥቃት እንደሆነ ይታመናል።
ክስተቱ በቻይና ብሔራዊ ቅሬታን የቀሰቀሰ ሲሆን ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ በበኩላቸው ወንጀል ፈጻሚው ግለሰብ “ከባድ ቅጣት” እንደሚጠብቀው ቃል ገብተው የተጎዱትን ለማከም “ሁሉን አቀፍ ጥረት” እንዲደረግ ጠይቀዋል።
ፖሊስ እንደገለጸው ከሆነ ሰኞ ዕለት አንድ ግለሰብ ዙሃይ በሚገኘው ስታዲየም የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ሰዎችን በመኪናው ገጭቷል።
“በአስከፊው እና በአሰቃቂው ጥቃት” አዛውንቶች እና ህጻናትን ጨምሮ 45 ሰዎችም መቁሰላቸውን የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
ፖሊስ እንዳለው ከሆነ የ62 ዓመቱ አሽከርካሪ ፋን እንደሚባልና ድርጊቱን የፈጸመው በፍቺው ውሳኔ ዙሪያ ደስተኛ ባለመሆኑ የተነሳ ይመስላል ።
ግለሰቡ ከዙሃይ ስፖርት ማዕከል ለመሸሽ ሲሞክር በቁጥጥር ስር መዋሉን እና በራሱ ላይ ባደረሰው ጉዳት ኮማ ውስጥ እንደሚገኝ ፖሊስ በመግለጫው አክሏል።
ስለተገደሉት ሰዎች ዝርዝር መረጃ በባለሥልጣናት በኩል አልተገለጸም።
ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮጵያዊያን
ህዳር 4 ቀን 2017 ዓ.ም
