የአዲስ አበባ ከተማ እና ዙሪያዋ ያለው የፀጥታ ሁኔታ አስተማማኝ ነው ሲል የፀጥታና ደኅንነት ጥምር ኃይሉ ገልፃል፡፡
የፀጥታና ደኅንነት ጥምር ኃይል በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ዋና መሥሪያ ቤት በአፈፃፀሙ ላይ ባካሄደው ግምገማ የአዲስ አበባ ከተማ እና ዙሪያዋ የፀጥታ ሁኔታ አስተማማኝ መሆኑን አረጋግጫለው ብሏል።
የፀጥታና ደኅንነት ጥምር ኃይል ታህሳስ 1 ቀን 2017 ዓ.ም ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት በአዲስ አበባ ከተማና ዙሪያዋ ያለውን የፀጥታ ሁኔታን ገምግሞ በአጠቃላይ እንደ ሀገር በሁሉም ክልል በተቀናጀ መልኩ እየተሰራ ባለው የፀጥታ ስራ ከፍተኛ ውጤት መገኘቱን አንስቶ፤ በተለይም በኦሮሚያ እና በአማራ ክልል በኮማንድ ፖስት እየተመራ በተከናወነ የፀጥታ ስራ እና በዙሪያዋ በተካሄደው ተከታታይ ኦፕሬሽን አሁን ላይ ህብረተሰቡን ስጋት ውስጥ የሚከቱ በጦር መሣሪያ በመታገዝ ተደራጅተው የሚፈፀሙ ወንጀሎች አለመኖራቸውን የፀጥታና ደኅንነት ጥምር ኃይሉ ማረጋገጡን አስታውቋል፡፡
በተመሳሳይ በአዲስ አበባ ከተማና ዙሪያዋ የፀጥታ ሁኔታን አስተማማኝ ለማድረግ ተካሂዷል ባለው ኦፕሬሽን በህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር፣ በኮንትሮባንድ፣ በህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር፣ በሀሰተኛ ሰነዶች፣ በእገታ እና በስርቆት ወንጀል ህብረተሰቡን ሲያማርሩ የነበሩ በርካታ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ጥምር ኃይሉ አስታውቋል፡፡
በተጨማሪም ሀገራችንን የአደገኛ ዕፅ ዝውውር መዳረሻ ለማድረግ በህገ-ወጥ መንገድ ወደ ሀገር ውስጥ በመግባት በአዲስ አበባ ከተማ ቤት ተከራይተው ሲሰሩ የነበሩ ስምንት የውጪ ሀገር ዜጎች እና አስራ አምስት ኢትዮጵያዊያን አምስት ኪሎ ኮኬይን አደገኛ ዕፅ፣ የሚዋጡ 189 የታሸገ ኮኬይን፣ የዕፁ ማሸጊያና መጠቅለያ ማሽን፣ የዕፁ መመዘኛ አነስተኛ ሚዛን እና በርካታ ዕፁን ለማሸግ ከሚያገለግሉ ቁሶች ጋር ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተጣራባቸው እንደሚገኝ ጥምር ኃይሉ ገልጿል።
ታኀሣሥ 17 ቀን 2017 ዓ.ም
