የአርብቶ አደሮች መሬት ሲወሰድ ካሳ አይከፈላቸዉም ተባለ፡፡

የአርሶ አደር መሬት ምዝገባ የሚካሄድ ቢሆንም፤ የአርብቶ አደሩ መሬት ምዝገባ ግን አለመጀመሩ ነዉ የተገለጸዉ፡፡

የመሬት ባለቤትነት ማረጋገጫ ስለሌላቸዉ አብዛኛዉ መሬታቸዉ ለፓርኮች ግንባታ እንዲሁም ለሌሎች ፕሮጀክቶች በሚል ቢወሰድም ምንም ዓይነት ካሳ እንደማይሰጣቸዉ ተገልጿል፡፡

መሬት በአግባቡ አይጠቀሙም፣ መሬት እንዲሸረሸር ያደርጋሉ እንዲሁም አርብቶ አደሩ በሚኖርበት አከባቢ ግጭት ይኖራል በሚል ምክንያት የመሬት ምዝገባ እንደማይደረግ በዩኤስ ኤድ የጋራ መሬት ይዞታ ስፔሻሊስት የሆኑት ዶክተር ዋቅቶሌ ኡማ ተናግረዋል፡፡

የመሬት ባለቤትነት ምዝገባ እንዲካሄድ በአንድ ቦታ ረግተዉ ወደ እርሻ መግባት አለባቸዉ የሚል መከራከሪያም ይነሳል ነዉ ያሉት፡፡

የንብረት መብት ህግ ቢኖርም ህጉ ተግባራዊ አለመሆን አርብቶአደሮች ከመሬታቸዉ ማግኘት የሚገባቸዉን ካሳ እንዳያገኙ አድርጓል ብለዋል፡፡

ክፍት መሬቶች ሲገኙ ለአርብቶ አደሩ ከመስጠት ይልቅ መሬቱን ለሌላ አላማ ማዋል ላይ ትኩረት መደረጉ ወደፊትም የሚቀጥል ትልቅ ችግር ነዉ ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በቦረና እና ምስራቅ ባሌ አከባቢዎች የአርብቶ አደሩን መሬት የመመዝገብ ስራዎች መሰራታቸዉን የገለጹት ዶክተር ዋቅቶሌ፤ በቦረና 2.7 ሚሊየን ሄክታር እና በምስራቅ ባሌ ደግሞ ከ6መቶ21ሺህ በላይ ሄክታር መሬት መመዝገቡን አንስተዋል፡፡

ግልጸኝነት የጎደለዉ የመሬት መቀራመት ሰዎች ከመኖሪያቸዉ እንዲፈናቀሉ፣ የኑሮ ሁኔታቸዉ ችግር ዉስጥ እንዲገባ እና ግጭት እንዲከሰት ማድረጉንም ዶክተር ዋቅቶሌ ገልጸዋል፡፡

እስከዳር ግርማ

ታኀሣሥ 18 ቀን 2017 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *