“ጠቡ ፣ ጥላቻው፣ መለያየቱ፣ መጠፋፋቱ፣ ለወንድሜ ከማለት ይልቅ ለኔ ለኔ ማለቱ ሲጎዳን እንጂ ሲጠቅመን ኣላየንም፡፡ አሁንም ወደ ልባችን እንመለስና በፍቅር፣ በዕርቅና በእኩልነት፣ በስምምነትና በወንድምነት ወደሚገኝ አንድነት እንምጣ፤ የልደቱ መዝሙር ያስተማረን ይህና ይህ ብቻ ነውና ” -ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላለፉ

ቅዱስነታቸው በመልእክታቸው “በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፤ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፤የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ፤በሕመም ምክንያት በየፀበሉና በየሆስፒታሉ ያላችሁ፤እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ሆናችሁ በየማረሚያ ቤቱ የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያት በሙሉ እንኳን ለሁለት ሺሕ ዐሥራ ሰባት ዓመተ ምሕረት የልደት በዓል በሰላም አደረሰን አደረሳችሁ ያሉ ሲሆን አምላክ ከሰውነታችን ጋር ባለመለያየት፣ ባለመጠፋፋት፣ ባለመቀላቀል፣ ባለመዋዋጥ፣ ባለመለዋወጥና ያለባዕድና አንድ አካል፣ አንድ ክዋኔ፣ አንድ ጠባይ ሆኖ በተዋሕዶ ተገልጾኣልና እግዚአብሔር ይክብር ይመስገን” ብለዋል።

ቅዱስነታቸው አክለውም ” እግዚአብሔር በእጅጉ ይወደናል ስንል እንዲሁ ከሜዳ ተነሥተን ኣይደለም፡፡ በበደላችንና በኃጢአታችን ሳይጸየፈን ሰውነታችንን በረድኤት ወይም በኅድረት ያይደለ በኩነት ተዋሕዶ ወደ አምላክነት ደረጃ ከፍ ስላደረገው ነው እንጂ፡፡ እግዚአብሔር በዚህ ፍጹምና ምሉእ ፍቅሩ ሰውነታችንን በመበረ ጸባኦት ኣስቀምጦ መላእክት ሳይቀሩ ፍጥረታትን በሙሉ እንድንገዛ አድርጎናል፤ ምክንያቱም መላእክት በዕለተ ልደት የዘመሩለት በተዋሕዶ አምላክም ሰውም ለሆነ ለቤተ ልሔሙ ሕፃን እንጂ ለመለኮት ብቻ ኣይደለምና ነው፡፡ የዕለተ ልደት መዝሙር ዛሬም በሰማያትም ሆነ በምድር በተዋሕዶ ሰውም ኣምላክም የሆነ አንዱ ኢየሱስ ክርስቶስ ይመለክበታል፣ ይመሰገንበታል፡፡የሰማዩና የምድሩ ዕርቅ ወደ ኋላ ላይመለስ ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በዚህ ተከናውኖኣል፣ የእግዚአብሔር ፈቃድ የሰውም አዋጭ ምርጫ ይህ ዕርቅ ተጠብቆ እንዲኖር ነው፣ ያለ ዕርቅ ሰላም ሕይወት የለውምና” በማለት ለምእመናን አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

“የእግዚአብሔር ክብርና ሰላም በእጅጉ የተሳሰሩና የተቆራኙ ናቸው፤ እኛ እግዚአብሔርን ካከበርነው፣ ካዳመጥነው፣ ከታዘዝነውና ከተከተልነው ሰላም አለ ማለት ነው፡፡ ለሱ ካልታዘዝንና እሱን ካላከበርን ግን ዘላቂ ሰላምን ማግኘት ፈጽሞ የማይታሰብ ነው፤ ምክንያቱም ሰላምን ጨምሮ መልካም ነገር ሁሉ ያለው በእግዚአብሔር እጅ ነውና፡፡ ዛሬ በሁሉም የዓለማችን ማዕዘን የሚታየው የሰላም መደፍረስ እግዚአብሔርን ካለማክበራችንና ለሱ ካለመታዘዛችን የተነሣ እንደሆነ መዘንጋት የለብንም፡፡ ዓለም ከእግዚአብሔር ቃል ርቃ ለመሄድ በእጅጉ እየኳተነች ነው፤ በዚህ እኩይ ተግባርዋ ደግሞ እግዚአብሔር ለስጋትና ለጉስቁልና አሳልፎ እየሰጣት ነው፡፡ እግዚአብሔር በምስጢረ ሥጋዌው ቢታረቃትም ዕርቁን ማክበር አቅቶአታል፤ ይህንን የእግዚአብሔር ጸጋ ቸል ብላ የምታደርገው ሩጫ የትም ሊያደርሳት እንደማይችል ብታውቅና በንስሓ ብትመለስ እግጅ ተጠቃሚ ትሆናለችምብለዋል።

“የእግዚአብሔር ቃል “እናንተስ ከማይጠፋ ዘር ተወለዳችሁ” ብሎ ተስፋውን እንደነገረን ምድባችን ከማይጠፋ ዘር እንዲሆን ክርስቲያኖች የሆን ሁላችን በአእምሮ ጐልብተን፣ በሥነ-ምግባር ኣምረን፣ ጤናማ ሕይወትን ልንመራ ይገባናል ያሉ ሲሆን የአምላካችንን በዓለ ልደት ስናከብር ነገረ እግዚአብሔርን፣ ነገረ ፍቅርን፣ ነገረ ዕርቅንና ነገረ ሰላምን በማኅበረሰባችን የማሥረጽ አጀንዳ ይዘን ልናከብር ይገባል፡፡

ጠቡ ፣ ጥላቻው፣ መለያየቱ፣ መጠፋፋቱ፣ ለወንድሜ ከማለት ይልቅ ለኔ ለኔ ማለቱ ሲጎዳን እንጂ ሲጠቅመን ኣላየንም፡፡ አሁንም ወደ ልባችን እንመለስና በፍቅር፣ በዕርቅና በእኩልነት፣ በስምምነትና በወንድምነት ወደሚገኝ አንድነት እንምጣ፤ የልደቱ መዝሙር ያስተማረን ይህና ይህ ብቻ ነውና፡፡ በሌሎቹ ክፍለ ዓለማት እንደሆነው ሁሉ በሀገራችን የተከሠተው አላስፈላጊ ግጭት ብዙዎችን አሳጥቶናል፤ ብዙዎችንም ከቤት ንብረታቸው አፈናቅሎ ሜዳ ላይ ፈሰው የሰቆቃ ኑሮ እንዲገፉ አድርጎብናል፡፡ የሀገር ሀብት እንዲወድም ሆኖአል፤ ልጆቻችን ምናለ ከእንግዲህ ወዲህ ቢበቃንና ምድሪቱን የሰላም አየር እንድትተነፍስ ብንፈቅድላት፤ ይህ የወቅቱ የቤተክርስቲያናችን ዋነኛ መልእክትና ጥሪ ነው” ፤ “በዓለ ልደት የእግዚአብሔር በዓል ነውና፣ እግዚአብሔር በምድራችን ሰላምን ያወርድ ዘንድ ካለን ከፍለን ለተፈናቃዮች፣ ለነዳያን እና ለአካል ጉዳተኞች በመለገስ በዓሉን በመንፈሳዊ ደስታና በሰላም እንድናከብር አባታዊ መልእክታችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን” በማለት አባታዊ የእንኳን አደረሳችሁ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

ታኀሣሥ 28 ቀን 2017 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *