ከኢትዮጵያ ዉጭ የተወለዱ እና የልደት ምዝገባ አከናውነዉ የመጡ ተመዝጋቢ ተማሪዎችን አንዳንድ ትምህርት ቤቶች ማስረጃቸዉን ለመቀበል ፍቃደኛ አለመሆናቸዉን ሰምተናል፡፡
በተለይ ከአረብ አገራት የሚመጡ ልጆች እዚህ አገር የተመዘገበ ካልሆነ በቀር ከዛ ይዘዉ የመጡትን የልደት ምዝገባ ማረጋገጫ ትምህርት ቤቶች ሊቀበሏቸዉ እንዳልቻሉ ነዉ የተገለጸዉ፡፡
የአዲስ አበባ የሲቪል ምዝገባ እና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናስ አለማየሁ ለኢትዮ ኤፍኤም እንደተናገሩት፤ በሌላ አገር የተመዘገበ የልደት ማረጋገጫ እዚህ አገር ላይ አይሰራም ተብሎ ስለሚታሰብ ጉዳዩን አስቸጋሪ አድርጎታል ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ የተመዘገበ የልደት ማረጋገጫ ወረቀት ካልሆነ በቀር ከሌላ አገራት የመጡ ማስረጃዎችን አንቀበልም ያሉ ትምህርት ቤቶችን ለማነጋገር እና ችግሩን ለመፍታት ሞክረናል ነዉ ያሉት፡፡
የልደት ምዝገባ አንድ ጊዜ የሚካሄድ በመሆኑ በየትኛዉም አገር የተመዘገበ ማስረጃ የትኛዉም ቦታ ላይ መስራት የሚችል ነዉ ሲሉ ዳይሬክተሩ ነግረዉናል፡፡
በስደተኛ ካምፖች ጭምር ለሚወለዱ ልጆች የልደት ምዝገባ አገልግሎት ይሰጣል የሚሉት ዳይሬክተሩ፤ በተለያዩ ምክንያቶች ሳያስመዘግቡ የሚቀሩ ሊኖሩ እንደሚችሉም አንስተዋል፡፡
ከዚህ በፊት የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከአረብ አገራት የተመለሱ ህጻናት ትምህርት ቤት ለመመዝገብ የልደት ካርድ እና የክትባት ወረቀት እንደሚጠየቁ አንስቶ ፤መሰረታዊ አገልግሎት ለማግኘት እየተቸገሩ ነዉ ሲል ለጣቢያችን አስታዉቆ እንደነበር ይታወሳል፡፡
እስከዳር ግርማ
ጥር 15 ቀን 2017 ዓ.ም
