ሱዳን እና ሩሲያ በቀይ ባህር ዳርቻ የባህር ሃይል ጦር ሰፈር ለመመስረት የመጨረሻ ስምምነት ማድረጋቸዉ ተገለጸ፡፡

በጦርነት እየታመሰች የምትገኘዉ ሱዳን ከሩሲያ ጋር በቀይ ባህር ዳርቻ የባህር ሃይል ጦር ሰፈር ለማቋቋም የመጨረሻ ስምምነት ላይ መደረሱን ተናግራለች።

በቀድሞው ፕሬዚደንት ኦማር አልበሽር የስልጣን ዘመን ወቅት በጉዳዩ ዙሪያ ውይይት ተደርጎ የነበረ ቢሆንም፤ እሳቸውን የገለበጠዉ ወታደራዊ መንግሥት ግን ጉዳዩ እየተገመገመ ነው ብሎ ነበር፡፡

የሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሊ የሱፍ ውል እንደተፈረመ እና ከሩሲያ ጋር በወደቡ ምስረታ ላይ “ሙሉ ስምምነት” ላይ መደረሱን ተናግረዉ፤ የቀረው ስምምነቱን ማፅደቅ ብቻ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ዉጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከሩሲያ አቻቸው ሰርጌ ላቭሮቭ ጋር በሞስኮ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ፤ሱዳን እና ሩሲያ የሩሲያን የባህር ኃይል ጦር ሰፈርን በሚመለከት ስምምነት ላይ ደርሰዋል ብለዋል።

ጉዳዩ በጣም ቀላል ነዉ፤በሁሉም ነገር ተስማምተናል ከማለት በስተቀር ዉጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ተጨማሪ ማብራሪያ አልሰጡም፡፡

ሞስኮ በፖርት ሱዳን አቅራቢያ የጦር ሰፈር ለማቋቋም ለዓመታት ስትፈልግ ብትቆይም፤የሩሲያዉ ዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ግን በጉዳዩ ላይ ምንም አስተያየት አልሰጡም፡፡

ስምምነቱ በ2019 ውይይት ተደርጎበት በ2020 የተፈረመ ቢሆንም፤ በ2023 ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ በኋላ ግን ዉሳኔዉ ግልጽ አልነበረም፡፡

ለ25 ዓመታት ይቆያል ተብሎ የታሰበዉ የወደብ ስምምነት ሩሲያ የባህር ኃይል ሎጂስቲክስ ማዕከል እንድትመሰርት፣ የጦር መርከቦች እና በኒውክሌር ኃይል የሚንቀሳቀሱ መርከቦችን እንድታሰማራ እና እስከ 3መቶ የሚደርሱ ሠራተኞችን እንዲይዝ የታቀደ ነበር፡፡

እስከዳር ግርማ

የካቲት 6 ቀን 2017 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *