የኦማን ተወላጁ የእስላማዊ መንግስት መሪ ተብሎ የሚታወቀዉ አህመድ ማኤሌኒን፤ በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ በሶማሊያ ፑንትላንድ ግዛት ውስጥ በአሜሪካ የአየር ጥቃቶች መገደሉን የፑንትላንድ ባለስልጣናት አስታዉቀዋል፡፡
በፈረንጆቹ የካቲት 1 ከፊል ራስ ገዝ በሆነችዉ ግዛት ዉስጥ በሚገኙ የአይ ኤስ ምሽጎች ዉስጥ በተደረገ ዘመቻ የጥቃቱ ዋና አላማ እርሱ እንደነበር ተገልጿል፡፡
በዓለም አቀፍ ወንጀሎች ሲፈለግ የነበረዉ ማኤሌኒን ላለፉት ሁለት አመታት በአከባቢው ተራሮች ተደብቆ በክትትል ስር መቆየቱ ነዉ የተገለጸዉ፡፡
እሱ ከሶማሌ እና ከአለም ህዝብ ሥጋ የተወገደ እሾህ ነዉ ሲሉ አንድ የፑንትላንድ ባለስልጣን ተናግረዋል፡፡
የዩኤስ አፍሪካ ኮማንድ (AFRICOM) ማኤሌኒን እና ሌሎች 13 የአይኤስ ታጣቂዎች መገደላቸውን ያረጋገጠ ሲሆን፤ ጥቃቱ ከሶማሊያ መንግስት ጋር በቅንጅት ተከናውኗል ብሏል።
ኮማንዱ፤ ጂሃዲስቶችን ወደ አሜሪካ እና አውሮፓ የመላክ ሀላፊነት የነበረዉ “መልማይ፣ ገንዘብ ሰጪ እና የውጭ ኦፕሬሽን መሪ” ነበር ሲል ገልፆታል።
እስከዳር ግርማ
የካቲት 6 ቀን 2017 ዓ.ም
