የመንገድ፣ የመብራትና የውሃ አቅርቦት ያልተሟላላቸው አካባቢዎች ዜጎች ቤታቸውን ተረክበው የማይኖሩበት እንዲሁም የሚኖሩትም ተደጋጋሚ ቅሬታ የሚያቀርቡበት ችግር እንደሆነ ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡
የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን መስከረም ላይ ባወጣው መግለጫ በእጣ ደርሷቸው እንዲሁም በጨረታ አሸንፈው ቤቶቹን ከተረከቡ በኋላ ያልገቡባቸውን ሰዎች ውላቸውን አቋርጣለሁ ብሎ እንደነበር ይታወሳል፡፡
ይሄን ተከትሎ ግለሰቦች ቤታቸው እንዳይወረስ በሚል ብቻ ቤታቸው እንደገቡ ለኢትዮ ኤፍ ኤም ተናግረዋል፡፡
የአዲስ አበባ ቤቶች ኮርፖሬሽን የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር ልሳነወርቅ ከልለው፤ በቅድሚያ ቤቶቹ ከባለቤቶቹ ጋር ይገናኙና የጎደሉትን እያሟሉ መሄድ የተሻለ አማራጭ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
መንግስት ቤቶችን እያስገነባ የመኖሪያ ቤት ችግርን ለመቅረፍ ጥረት እያደረገ ቢሆንም፤ አሁንም የሚታዩ ጉድለቶች አሉ ሲሉ የጋራ መኖሪያ ቤቶቹን ተረክበው የሚኖሩ ነዋሪዎች ይገልፃሉ፡፡
የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተሩ፤ቤቶቹን ዘግቶ ማቆየት ለተለያዩ ህገወጥ ተግባራት የሚጋብዝ ነዉ ይላሉ፡፡
ለዚህም እንደ አራብሳ፣ ቦሌና አያት ባሉ ሳይቶች ላይ ቅሬታዎቹን መሠረት አድርገው እየሰሩ እንደሆነም ነዉ የገለጹት፡፡
የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን መስከረም ላይ ባወጣው መግለጫ በእጣ ደርሷቸው እና በጨረታ አሸንፈው ቤቶቹን ከተረከቡ በኋላ ያልገቡ ነዋሪዎችን እስከ ጥቅምት 30 መግባት ካልቻሉ ዉላቸዉን እንደሚያቋርጥ ገልጾ እንደነበር የሚታወስ ነዉ፡፡
አፎሚያ አሸናፊ
የካቲት 11 ቀን 2017 ዓ.ም
