በትግራይ ለስነ አይምሮ ህክምና የሚረዱ መድኃኒቶች ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ ቢጨምርም መድኃኒቶቹን ማግኘት አልተቻለም ተብሏል።
በክልሉ አሁን ላይ በከፍተኛ ሁኔታ የስነ አዕምሮ መድሀኒት ፍላጎት መጨመሩን የነገሩን በአይደር ሆስፒታል የፋርማሲ ክፍል ዋና ሀላፊው አቶ ጣዕመ አረጋዊ ናቸው።
ሀላፊው፤ በተለይም መድሀኒቱን ከመድሀኒት አቅራቢ አገልግሎት ብንጠይቅም የአገልግሎቱ ምላሽ ግን በሚፈለገው ልክ እንደሌለ ተናግረዋል።
በቀን ወይም ደግሞ በወር መድሀኒቱ በትንሽ መጠን ቢመጣም ለታካሚዎች በሚፈለገው ልክ መድረስ እንዳልቻሉ አቶ ጣዕመ ነግረውናል።
የስነ አዕምሮ መድሀኒት በጣም አስፈላጊ እና በሚፈለገው ሰዓት መገኘት ያለበት ቢሆንም በትግራይ ግን ችግሩ ተሰፋፍቷል ተብሏል።
ሆስፒታሉ ያጋጠመውን የመድኃኒቶች እና የላብራቶሪ ግብዓቶች እጥረት ለመቅረፍ በፋርማሲ ባለሞያዎች ግመታ መሰረት እስከ 300 ሚሊየን ብር እንደሚያስፈልግም ገልፀዋል።
በክልሉ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ካለው የስነ አዕምሮ መድሃኒቶች ፍላጎት አኳያ አንዳንድ መድሃኒቶች በመድሃኒት አቅርቦት ድርጅት በኩልም እንደማይገኙ የተገለጸ ሲሆን ይህ ካልተፈታ በትግራይ ትልቅ ችግር ሊከሰት እንደሚችል ሀላፊው ስጋታቸውን ገልፀዋል።
ለአለም አሰፋ
የካቲት 28 ቀን 2017 ዓ.ም
