የዛምቢያው ፕሬዝዳንት ሃካንዴ ሂቺሌማ ሚኒስትሮቻቸውን በስብሰባ ወቅት እንዳያንቀላፉ አስጠንቅቀዋል፡፡
በፕሬዝዳንቱ እምነት ሚኒስትሮቻቸው በስብሰባ ወቅት ማንጎላጀታቸው “ቸልተኝነታቸውን” እና ራሳቸውን መቆጣጠር የተሳናቸው መሆናቸውን ያመላክታል።
ሂቺሌማ ይህንን የተናገሩት አዲስ ተሿሚ ሚኒስትር ኋላፊነታ ለመጀመር ቃለ መሃላ በፈፀሙበት ስነ ስርዓት ላይ ነው።
“ሰዎች በካቢኔ ስብሰባ ወቅት የሚያንቀላፉ ምሽቱን የት አሳልፈው ነው። ለእኔ ትልቅ ወንጀል ነው” ብለዋል።
እርሳቸው በትክክል ምን ለማለት እንደፈለጉ ባይገልጹም የሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሀን ይህንን ሲተረጉሙት ከመጠን በላይ አልኮል መጠጣት እና ምሽት ላይ ድግስ ማብዛትን ለማለት ነው ብለዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ እንዲህ አይነት ነገር የመንግስትን ሚስጥር እና የህዝብ አገልግሎት አሰጣጥን በእጅጉ አደጋ ላይ እንደሚጥል አስጠንቅቀዋል።
ሂቺሌማ በ2021 ከፍተኛ የህዝብ ድምጽ በማግኘት ሲያሸንፉ በአፍሪካ ሁለተኛዋ የመዳብ አምራች ሀገርን ወደ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ባለቤትነት ለመቀየር ቃል ገብተዋል፡፡
ፕሬዝደንቱ ወደ ስራ ከገቡ በኃላም ከደካማ የስራ በአፈፃፀም ጋር በተያያዘ ሚኒስትሮችን ጨምሮ በርካታ ከፍተኛ ባለስልጣናትን ከስራ አሰናብተዋል እንደ ቢቢሲ አፍሪካ ዘገባ፡፡
መጋቢት 24 ቀን 2017 ዓ.ም
