አሜሪካ እና ኢራን በኒውክሌር ስምምነት ላይ “ቀጥታ ውይይት” ሊያደርጉ ነው

አሜሪካ እና ኢራን በኒውክሌር ስምምነት ላይ “ቀጥታ ውይይት” ቅዳሜ ዕለት እንደሚጀምሩ ዶናልድ ትራምፕ ተናገሩ።

የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ውይይቱ እንደሚካሄድ አረጋግጠው፣ ውይይቱ የሚካሄደው “በተዘዋዋሪ ሊሆን ይችላል” ካሉ በኋላ “እድል የመሆኑን ያህል፣ ምን እንዳለ ለመቃኘት ይረዳል” ብለዋል።

የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳንት ሰኞ ዕለት በዋሽንግተን እና ቴህራን መካከል የሚደረገው ውይይት “በከፍተኛ ባለስልጣናት ደረጃ ነው” በማለት ተናግረው፣ ስምምነት ላይ ካልተደረሰ “ለኢራን በጣም መጥፎ ቀን ይሆናል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ባለፈው ወር የኢራን ከፍተኛ ሃይማኖታዊ መሪ አያቶላ አሊ ካሜኔይ አሜሪካ ያቀረበችውን የቀጥተኛ ንግግር ጥያቄ በይፋ ውድቅ ካደረጉ በኋላ ዶናልድ ትራምፕ በኢራን ላይ ወታደራዊ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚችል ተናግረው ነበር።

ትራምፕ ውይይት ለማድረግ ቀጠሮ መያዙን የተናገሩት ከእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ ጋር በኋይት ሀውስ ከተገናኙ በኋላ ነው።

ትራምፕ “ቅዳሜ ጋር በጣም ትልቅ ስብሰባ አለን፣ ከእነሱ ጋር በቀጥታ እንነጋገራለን… እና ምናልባት ስምምነት ሊደረስ ይችላል፣ ያ የሚሆን ከሆነ ጥሩ ነው” ብለዋል ።

ትራምፕ አክለውም ድርድሩ ካልተሳካ ኢራን “ትልቅ አደጋ” ውስጥ ትገባለች ሲሉ የተናገሩ ሲሆን፣ “ኢራን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ሊኖራት አይችልም፤ እና ውይይቱ ካልተሳካ በእውነቱ ለኢራን በጣም መጥፎ ቀን ይሆናል ብዬ አስባለሁ” ብለዋል ።

ፕሬዚዳንቱ የሚደረገው ንግግር በምን ደረጃ ላይ እንዳለ እንዲሁም የትኞቹ ባለስልጣናት እየተሳተፉ እንደሆነ ከመናገር ተቆጥበዋል።

የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋሽንግተን እና ቴህራን ሚያዝያ 4/ 2017 ዓ.ም. በኦማን እንደሚገናኙ አረጋግጠዋል።

አባስ አራክቺ በኤክስ ገጻቸው ላይ “ያለውን የምንፈትሽበት የመሆኑን ያህል እድልም ነው፤ ኳሱ በአሜሪካ ሜዳ ውስጥ ነው” ብለዋል።

መጋቢት 30 ቀን 2017 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *