ዶናልድ ትራምፕ ተጨማሪ 50% ታሪፍ ቻይና ላይ ለመጣል ዝተዋል። ቻይና በበኩሏ ‘እስከመጨረሻው’ ለመታገል ቃል ገብታለች፡፡
ቻይና ወደ አሜሪካ የምትልካቸው ሸቀጦች ላይ ቻይና የጣለችው 34% ታሪፍ የማይነሳ ከሆነ ተጨማሪ 50% ታሪፍ ቻይና ላይ እንደሚጥሉ አስታውቀዋል።
ቻይና ይህንን የትራምፕን ማስፈራሪያ ‘ከስህተት በላይ የሆነ ስህተት’ ብላ ጠርተዋለች፡፡
ቻይና ንግድ ሚኒስቴር የአሜሪካን ውሳኔ ፈጽሞ እንደማይቀበል ተናግሯል፡፡ “እስከ መጨረሻው” ለመዋጋትም ቃል ገብቷል፡፡
ሚኒስቴሩ የፕሬዝዳንት ትራምፕን ዛቻን “ከስህተት በላይ የሆነ ስህተት” ብሎታል።
ሁሉም የታሪፍ እቅዶች እንዲወገዱ እና የአሜሪካ እና ቻይና ልዩነቶች በውይይት እንዲፈቱ ጠይቋል።
ባለፈው ሳምንት ቻይና ላይ ለጣሉት ታሪፍ በምላሹ ቻይና 34% ታሪፍ እንደምትጥል አስታውቃለች። ትራምፕም ቻይና የጣለችውን የአጸፋ ታሪፍ እስከ ማክሰኞ ድረስ ካላነሳች 50% ተጨማሪ ታሪፍ እንደሚጥሉ አስጠንቅቀዋል።
ትራምፕ የጣሉትን ታሪፍ በተመለከተ በአሜሪካ የቻይና ኤምባሲ “የምጣኔ ሀብት ጭቆና ነው። መብታችንን ከማስጠበቅ ወደኋላ አንልም” ሲል ምላሽ ሰጥቷል።
ትራምፕ ተጨማሪ 50% ታሪፍ ቻይና ላይ ከጣሉ የአሜሪካ ተቋማት ከቻይና የሚያስገቡት ምርት በአጠቃላይ 104% ታሪፍ የተጣለበት ይሆናል።
የቤጂንግ የመንግስት ጋዜጣ ፒፕልስ ዴይሊ “ግፊት እና ዛቻዎች በእርግጠኝነት ከቻይና ጋር ለመነጋገር ትክክለኛው መንገድ አይደሉም” በሚል ርዕስ ባወጣው ዘገባ የትራምፕ አስተዳደርን ተችቷል፡፡
የቻይና የውጭ ንግድ በጫና ውስጥ ጥንካሬን አሳይቷል፣የቻይና ኢኮኖሚ ሁሌም ልማትና እድገትን አስጠብቆ ቆይቷል።በአንፃሩ ዩናይትድ ስቴትስ የንግድ ጉድለቶችን የመቀነስ እና የማኑፋክቸሪንግ ግቦችን ማሳካት ባለመቻሏ ብቻ ሳይሆን በራሷ ኩባንያዎች እና ሸማቾች ላይ ኪሳራ አድርሷል።”ሲልም ገልጻል፡፡
ይህም የዓለም ሁለት ትልቅ ምጣኔ ሀብት አገራትን የንግድ ጦርነት እንዳያባብስ ተሰግቷል።
ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል ገጻቸው “ከቻይና ጋር ስለ ታሪፍ እንድንነጋገር የተያዘው ዕቅድ ተሰርዟል” ማለታቸው ተዘግቧል፡፡
መጋቢት 30 ቀን 2017 ዓ.ም
