በክረምቱ የዝናብ ወቅት ሊደርሱ የሚችሉ አደጋዎችን በመለየት የቅደመ ዝግጅት ስራዎች እየሰራ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የእሳት እና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታውቋል፡፡
የአዲስ አበባ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከሌሎች ተቋማት ጋር የተሰሩ ቅንጅታዊ አሰራሮችን እየገመገመ ባለበት መድረክ ነው ይህን ያስታወቀው
የጎርፍ አደጋ ፣የመሬት መንሸራተት እንዲሁም ከኤሌክትሪክ ጋር ተያይዞ የሚደርሱ ቃጠሎዎች በክረምት ወቅት ዋነኛ የአደጋ መንስኤ ሆነዉ እንደተለዩ ተነስቷል ።
ከጎርፍ ጋር ተያይዞ የዉሃ ማፋሰሻዎችን ንፅህናቸዉን መጠበቅ ፣የተደፈኑ ካሉ የመክፈት እንዲህም ግንባታ የሚያስፈልጋቸዉ ቦታዎችን የመገንባት ስራዎች እየተሰሩ መሆኑንም ኮሚሽኑ አስታውቋል ፡፡
በከተማ አስተዳደሩ የመሬት መንሸራተት የሚያጋጥማቸዉ ቦታዎች የተለዩ ሲሆን፤ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራበት መሆኑ ተገልጿል፡፡
ሶስት መቶ የሚደርሱ አደጋዎች ተለይተው፤ 1 መቶ 70 ለሚሆኑት መፍትሄ እንደተሰጠ የእሳት እና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታውቋል ፡፡
አቤል እስጢፋኖስ
ሚያዚያ 01ቀን 2017 ዓ.ም
