የቻይና ባለስልጣናት ሰሞኑን ዶናልድ ትራምፕ በአገራቸው ላይ የጣሉትን ተጨማሪ ታሪፍ ተከትሎ አሜሪካ ይህንን ውሳኔዋን ሙሉ በሙሉ እንድትሰርዝ አስጠንቅቀዋል።
ዶናልድ ትራምፕ በአገራት ላይ ሊጥሉት ያቀዱትን ታሪፍ ለ90 ቀናት እንዲዘገይ በዚህ ሳምንት አሳውቀዋል። በአንጻሩ በቻይና ምርቶች ላይ የሚጥሉትን ታሪፍ ደግሞ ወደ 145% ከፍ አድርገዋል።
“አሜሪካ ስህተቷን ለማረም ትልቅ ርምጃ እንድትወስድ ለማስጠንቀቅ እንወዳለን፤ የተሳሳተ አካሄድ የሆነውን የአጸፋ ታሪፍ ጭማሪ በመሰረዝ ትክክለኛውን የጋራ ተጠቃሚነት መንገድ መመለስ ይገባል” ብሏላ የቻይና የንግድ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ።
ባለፈው አርብ ዶናልድ ትራምፕ ቻይና የሚመረቱ የተወሰኑ የኤሌክትሮኒክስ ምርቶችን ከታሪፍ ነጻ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን አሳውቀዋል።
ነገር ግን የአሜሪካው የንግድ ሚኒስትር ሐዋርድ ሉትኒክ ባለፈው እሁድ እንዳሉት እንደዚህ ዓይነቶቹ ውሳኔዎች ለአጭር ጊዜ ብቻ የሚቆዩ ናቸው።
በእነዚህ ምርቶች ላይ በተለየ ሁኔታ የታሪፍ ጭማሪ የሚደረግ ሲሆን፣ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ጭማሪው ይፋ ይደረጋል ብለዋል።
“እነዚህ ምርቶች በአሜሪካ እንዲሠሩ እንፈልጋለን” ሲሉ ሚኒስትሩ ተደምጠዋል ሲል
ቢቢሲ ዘግቧል።
ሚያዚያ 06 ቀን 2017 ዓ.ም
