የኑሮ ውድነት የበረታባቸው የኢትዮጵያ አስተማሪዎችን ለመርዳት ይቋቋማል የተባለው “የመምህራን የኅብረት ሥራ ባንክ” በሚቀጥለው ዓመት ሥራ ሊጀምር እንደሚችል የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሀኑ ነጋ ፍንጭ ሰጡ።
መንግሥት ለአስተማሪዎች ለቤት መሥሪያ የሚሆን መሬት ቢያቀርብ የሚቋቋመው ባንክ በአነስተኛ ወለድ ብድር የሚሰጥ ይሆናል።
ፕሮፌሰር ብርሀኑ ባንኩ በሚቀጥለው ዓመት ሥራ ሊጀምር እደሚችል ተስፋቸውን የገለጹት ትላንት ማክሰኞ የትምህርት ሚኒስቴርን የ2017 የዘጠኝ ወራት የዕቅድ አፈጻጸም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡበት ወቅት ነው።
በትላንትናው የምክር ቤቱ ውሎ ከተነሱ ጉዳዮች መካከል በግጭት ምክንያት ከትምህርት ገበታ ውጪ የሆኑ ተማሪዎች ቁጥር እና ችግሩን እንዴት ይፈታል የሚለው ይገኝበታል።
ከትምህርት ቤት ውጪ የሆኑ ተማሪዎችን ቁጥር በተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት “እስከ 10 ሚሊዮን ያደርሰዋል” ያሉት ዶክተር ደሳለኝ ጫኔ “ቢያንስ ሰላም እስኪሰፍን ድረስ ምን እየተሠራ” እንደሆነ ጠይቀዋል።
ፕሮፌሰር ብርሀኑ ግን በተባበሩት መንግሥታት ሪፖርት የተጠቀሰውን ቁጥር “በፍጹም አላምንም” ሲሉ ተናግረዋል።
ቢሆንም “7.2 ሚሊዮን ልጆቻችን ትምህርት ቤት አለመግባታቸው በጣም በጣም ሊያሳስበን የሚገባ ጉዳይ ነው” ሲሉ ተደምጠዋል። የኢትዮጵያን ልጆች ከትምህርት ገበታ ያራቀው “ትልቁ” ምክንያት በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚካሔዱ ግጭቶች መሆናቸውንም አምነዋል።
ሚያዚያ 8 ቀን 2017 ዓ.ም
