ቋሚ ኮሚቴዉ ይህን ያለዉ የሰላም ሚኒስትር የዘጠኝ ወራቱን የስራ አፈፃፀም በገለፀበት ወቅት ነዉ።
ቋሚ ኮሜቴዉ በማሳያነት ያነሳዉ በማእከላዊ ኢትዮጵያ በሚገኙት የሀዲያ እና ጉራጌ ዞን ላይ የሚነሱ የአስተዳደር ወሰን ግጭቶችን ነዉ።
የህዝብ መብት እና የማንነት ጥያቄዎች እንዲፈቱ ጥያቄዎች መቅረባቸዉን ኮሚቴዉ አስታውቋል።
በተለያየ ጊዜም ለፌዴሬሽን ምክርቤት ይቀርባል ተብሎ ሳይፈታ መቆየቱ ችግር ይሆናል ሲል ቋሚ ኮሚቴዉ በመድረኩ ገልፆል።
ለቀረበዉ ጥያቄ ምላሽ የሰጡት የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ቸሩጌታ ገነነ እንደገለፁት በክልሎች የሚፈጠሩ ማንኛውም ግጭቶች ከክልሉ አቅም በላይ ሲሆን ነዉ ጣልቃ መግባት የምንችለዉ ብለዋል።
አያይዘዉም አሁን ላይ ግን ጉዳዩ የክልሉ መንግስት ከአቅሜ በላይ ነዉ አላለንም ብለዋል።
ሆኖም ለእኛ እየደረሱን ያሉ መረጃዎች ክልሉ መፍታት እንዲችል አሳዉቃለሁ ሲል የሰላም ሚኒስትር ገልፆል።
የሰላም ሚኒስትር ዴኤታዉ አቶ ቸሩጌታ ገነነ ተቋማቸዉ ከህዝብ ከደረሱት 347 የግጭት ጥቆማዎች 250 ትንንሽ ግጭቶችን ማስቆም መቻሉን ተናግረዋል።
አቶ ቸሩጌታ የዘጠኙን የስራ አፈፃፀም በገለፁበት ሪፖርት 380 ሺህ የሀገር ዉስጥ ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸዉ መመለስ መቻሉን ጠቅሰዋል።
1.9 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ወደ ቀያቸዉ ያልተመለሱ መሆኑን ሰምተናል።
ሚኒስትር መስሪያቤቱ ተፈናቃዮችን በመመለስ ረገድ የፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እያገኙበት ያሉ አካላት ለስራዬ እንቅፋት ሆነዋል ሲል አቅርቧል።
ቁምነገር አየለ
ሚያዚያ 21 ቀን 2017 ዓ.ም
