በየመንገዱ የምናያቸዉ እና ጽኑ የአዕምሮ ህመም የሚስተዋልባቸዉ ሰዎች ቁጥር ከ1በመቶ በታች መሆኑንም ሰምተናል፡፡
ከኢትዮ ኤፍኤም ጋር ቆይታ ያደረጉት የአዕምሮ ሀኪም እና የአዕምሮ ህክምና ማህበር ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር አታላይ ዓለም፤ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ከ 8 ሰዎች አንዱ ከትንሽ መረበሽ እስከ ከባድ የአዕምሮ ህመም ድረስ ያጋጥመዋል ብለዋል፡፡
በአገራችንም ይሄ ቁጥር ተመሳሳይ ነዉ ያሉት ፕሮፌሰሩ፤ አንድ ስምንተኛ የሚሆነዉ የአገራችን ህዝብ ለተለያዩ የአዕምሮ ህመሞች የተጋለጠ መሆኑን አንስተዋል፡፡
እንደ ፕሬዝዳንቱ ገለጻ፤ በአገራችን ጽኑ የአዕምሮ ህመም አለባቸዉ የሚባሉ ሰዎች ከ 1 በመቶ በታች ናቸዉ፡፡
ባይፖላር እንዲሁም ከበድ ያለ ድባቴ ያለባቸዉ ሰዎች ቁጥር ደግሞ ወደ 3 እና 4 በመቶ ከፍ ያለ ነዉ፡፡
በአገራችን በአብዛኛዉ የሚታየዉ እና ከፍተኛዉን ቁጥር የያዘዉ የአዕምሮ ህመም ዓይነት ጭንቀት እና ድባቴ መሆኑንም ፕሮፌሰር አታላይ ተናግረዋል፡፡
የአዕምሮ ህክምናን ተደራሽ በማድረግ በኩል ከ20 እና 30 ዓመት በፊት ከነበረዉ ሁኔታ ተሻሽሏል የሚሉት ፕሬዝዳንቱ፤ አሁንም የግንዛቤ ችግር መኖሩን ግን አልሸሸጉም፡፡
ህብረተሰቡ የአዕምሮ ህክምና አገልግሎት በየጤና ጣቢያዉ እንደሚሰጥ ባለማወቁ አማኑኤል ሆስፒታልን አልያም ሌሎች ተቋማትን ምርጫዉ ያደርጋል ብለዋል፡፡
በህክምናዉ ዙሪያ የግንዛቤ ችግር በመኖሩም የአገልግሎቱ ተደራሽነት ዉስን ሆኗል ሲሉ ለጣቢያችን ተናግረዋል፡፡
በዓለም ዓቀፍ ደረጃ አንድ ቢሊየን ሰዎች ከአዕምሮ ህመም ጋር እንደሚኖሩ የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ያመላክታል፡፡
እስከዳር ግርማ
ግንቦት 4 ቀን 2017 ዓ.ም
