የተባበሩት መንግስታት የመብት ሃላፊ ቮልከር ተርክ፤ የእስራኤል የጥቃት ዘዴዎች በፍልስጤማውያን ላይ አሰቃቂ እና የማይታሰብ ስቃይ እያደረሱ ነው ብለዋል።
ሀገሪቱ ከተቀናቃኟ ኢራን ጋር የሚሳኤል ጥቃት እየተለዋወጠች ባለችበት ወቅት እንኳን በፍልስጤማዊያን ላይ የምታደርሰዉን ጥቃት ያለማቋረጥ ቀጥላለች ብለዋል፡፡
ቮልከር ተርክ የእስራኤል የጦርነት መንገዶች በጋዛ ውስጥ ፍልስጤማውያን ላይ አሰቃቂ እና የማይታሰብ ስቃይ እያደረሱ ነው ብለዋል፡፡
ከ19 ወራት በላይ በቀጠለዉ የእስራኤል ጥቃት በሺዎች የሚቆጠሩ ህጻናትን ጨምሮ ቢያንስ 55 ሺህ3መቶ62 ሰዎች ህይወታቸዉ አልፏል፡፡
ዛሬ ማለዳዉን በአወዛጋቢዉ የጋዛ ሰብዓዊ ፋዉንዴሽን በሚተዳደረዉ እና በአሜሪካ እና እስራኤል በሚደገፈዉ የዕርዳታ ጣቢያ ድጋፍ ለመቀበል የተገኙ 15 ፍልስጤማዊያንን ጨምሮ 20 ሰዎች ተገድለዋል፡፡
በሰሜን ጋዛ ተጨማሪ ሶስት እርዳታ ፈላጊዎች መገደላቸው የተዘገበ ሲሆን፤ሁለቱ በጋዛ ከተማ ላይ በተፈጸመ ጥቃት መሞታቸው ተነግሯል።
ተርክ በጄኔቫ በተካሄደው 59ኛው የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት አመታዊ ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት ‹‹እስራኤል የህይወት አድን እርዳታን በማቋረጥ ምግብን እንደ ጦር መሳሪያ እየተጠቀመች ነዉ›› ማለታቸዉን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡
እስከዳር ግርማ
ሰኔ 9 ቀን 2017 ዓ.ም
