ተቋራጮችና የተቋራጭ አማካሪዎች ምዘና እና ደረጃ ይወጣላቸዋል ተባለ

ከተያዘዉ ዓመት ጀምሮ ዉጤታማና ተወዳዳሪ የሆኑ ተቋራጮችና አማካሪዎች እንዲሁም የመንግስት ፕሮጀክቶች ባለቤቶችን ለመለየት እንዲቻል ምዘናና ደረጃ ይወጣላቸዋል ተብሏል፡፡

‹‹የሃገር ዉስጥ የግንባታ ኢንደስትሪ ዘርፍ ተፎካካሪነት እና ምዘና ›› በተሰኘ መንገድ ነዉ ተመዝነዉ ደረጃ እንደሚሰጣቸዉ የተገለጸዉ፡፡

የከተማና መሰረተ ልማት ሚንስቴር ሚንስትር ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ፤የኮንስትራክሺን ዘርፍ የአፈጻጸም ደረጃ ለማሻሻልና የዘርፉን ጤናማነት እንዲሁም ብቃት ያለዉ ተወዳዳሪ የኮንስትራክሺን ኢንደስትሪ እንዲሆን እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የኮንስትራክሺን ኢንደስትሪ ምክርቤትን ጨምሮ የሚመለከታቸዉ የዘርፉ ተዋናዮች በግልም ሆነ ባማህበር ያሉ ባለድርሻ አካላት የበኩላቸዉን አስተዋጾ እንዲያበረክቱ ሚኒስትሯ ጠይቀዋል፡፡

ዘርፉ ግዙፍ ካፒታል የሚፈልግ፤በሃገርም ሆነ በዉጭ የሚመረቱ ግብዓቶችን የሚጠቀም፤ከፍተኛ የሆነ የሰለጠነ የሰዉ ሃይል የሚያስፈልገዉ፤ቴክኖሎጂዎችን የሚጠቀም እንደመሆኑ መጠን ከፍተኛ ትኩረትን ይፈልጋልም ሲሉም ሚኒስትሯ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

በዚህም በተቋራጮች እና በተቋራጭ አማካሪዎች ምዘናና ደረጃ እንደሚወጣ እንዲሁም ዉጤቱ ልህዝብ ይገለጻል ያሉት ሚኒስትሯ በሂደቱ ዉጤታማ የሆኑ ባለሙያዎች እዉቅና እና በጨረታ ወቅት የተለየ እድል የሚያገኙበት ሁኔታ ይመቻችላቸዋል ሲሉም ተናግረዋል፡፡

በሚቀጥሉት ጥቂት አመታትም ቢያንስ ወደ 20 ለሚጠጉ ዉጤታማ የግንባታ ተቋራጮችና አማካሪዎች በየዓመቱ የሚደረገዉን ግምገማና የደረጃ ሊየታን መሰረት በማድረግ በዉጭ ገበያ ላይ ሃገርን ወክለዉ ተወዳዳሪ ሆነዉ እንዲሰሩ ድጋፍ ይደረግላቸዋል ብለዋል፡፡

በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪዉ አጠቃላይ በፕሮጀክቶች አካሄድ ላይ ያለዉን ዉስብስብ ችግር የሚለይ መፍትሄ የሚሰጥ ማእቀፍ ፤‹‹ኢዝ ኦፍ ዱይንግ ቢዝነስ ኢን ኮንስትራክሺን ሴክተር›› ተግባራዊ ይደረጋልም ብለዋል፡፡

አሁን ባለዉ አካሄድ ዘርፉ በአሳሳቢ ደረጃላይ ይገኛል ያሉት ሚኒስትሯ ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ፤ዘርፉን ለማሻሻል ይደረጉ የነበሩ ጥረቶች በተበታተነ መንገድ በመሆኑ፤የዘርፉ ተዋናዮች ለዘርፉ እድገት የበኩላቸዉን አበርክቶ እንዳያደርጉ ችግር ሆኖ መቆቱን አንስተዋል፡፡

ሆኖም ዘርፉን ለማሳደግ አሁን ለሚደረገዉ ጥረት ዉጤታማነት እነዚህ ስራዎች በፖሊሲ እና ህጋዊ ማእቀፍ ኖሯቸዉ አፈጻተማቸዉ ወጥ እንዲሆን ቀድሞ የነበረዉ አሰራር በአዲስ ተቀይሮ በስራ ላይ እንደሚዉልም አንስተዋል፡፡

በተጨማሪም ከዚህ በፊት ያልነበረ ኮንስትራክሺን ኢንዱስትሪ አዋጂ በስራ ላይ ከሚገኘዉ የህንጻ አዋጅ ጋር ተቀናጂቶ፤ ኢንደስትሪዉንና የዘርፉን ስራዎች ዘመኑን በዋጀ መልኩ በማካተት በአጭር ጊዜ ዉስጥ በስራ ላይ ይዉላል ሲሉም ተናግረዋል፡፡

ልኡል ወልዴ

ሰኔ 20 ቀን 2017 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *