ባሳለፍነው ሳምንት በኢራን ዋና ከተማ ቴህራን እስራኤል ባደረሰችው የአየር ጥቃት በእስር ቤት ውስጥ የሚገኙ 71 ሰዋች መሞታቸው እና ብዙዎች መቁሰላቸውን ኢራን አስታዉቃለች።
የኢራን የፍትህ አካል ቃል አቀባይ እንደተናገሩት፤ በኢቨን እስር ቤት ላይ የተፈፀመው ጥቃት በእስራኤል ሃይሎች የተፈፀመ ወንጀል ነው ሲሉ አውግዘዋል።
ከሟቾች መካከል የእስር ቤቱ አስተዳደር ሰራተኞች፣ ወታደሮች፣ እስረኞች፣ የታሳሪ ቤተሰቦች እንዲሁም በእስር ቤቱ አካባቢ የሚኖሩ ንፁሃን መኖራቸውን ቃለ አቀባዩ አክለው ገልፀዋል።
የአየር ጥቃቱ ባሳለፍነው ሰኞ የእስራኤል ጦር በቴህራን ላይ በተለያዩ ኢላማዎች የከፈተው የአየር ጥቃት አካል እንደነበር የእስራኤል ባለስልጣናት ገልፀዋል።
ለ12 ቀናት የቆየው የኢራን እና እስራኤል ግጭት፤ሰኔ 13 እስራኤል በኢራን ወታደራዊ ፣ኒኩሌር እና ሲቪል ቦታዎች ላይ የአየር ጥቃት ካደረሰች በኋላ የተቀሰቀሰ ነው።
እንደ ኢራን ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር መረጃ መሰረት በግጭቱ 6መቶ6 ሰዎች ሲሞቱ 5ሺ3መቶ32 ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል፡፡
ቴህራንም ሚሳኤልና ድሮን በመጠቀም ለእስራኤል ጥቃት የአጸፋ ምላሽ የሰጠች ሲሆን፤ በዚህም ቢያንስ 29ሰዎች ሲሞቱ ከ3ሺህ በላይ መቁሰላቸው ተገልጿል፡፡
በሁለቱ ሃገራት መካከል ያለው ግጭት በአሜሪካ ድጋፍ ማክሰኞ ዕለት የቆመ ሲሆን ፤ የእርቅ ስምምነቱ የተደረሰው በኤቪን እስር ቤት ጥቃት ከተፈፀመ ከአንድ ቀን በኋላ ነዉ ሲል ሚድል ኢስት ሞኒተር ነዉ የዘገበዉ፡፡
ሀሚድ አብደላ
ሰኔ 23 ቀን 2017 ዓ.ም
