ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ ለውጭ ሰብዓዊ እርዳታ ትሰጥ የነበረውን የገንዘብ ድጋፍ መሰረዛቸው በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ተጨማሪ 14 ሚሊዮን ሰዎች ሕይወት እንዲያልፍ ሊያደርግ እንደሚችል ዘ ላንሴት የተባለው ተቋም የሕክምና ሪፖርት ጠቆመ።
ያለጊዜው ለሞት ከሚዳረጉት ውስጥ አንድ ሶስተኛውን የሚይዙት ህጻናት መሆናቸውን ጥናቱ አመልክቷል።
የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ በመጋቢት ወር የፕሬዚዳንት ትራምፕ አስተዳደር በዩኤስ ዓለም አቀፍ ልማት ኤጀንሲ ወይም ዩኤስኤአይዲ ከ 80በመቶ በላይ ፕሮግራሞችን መሰረዛቸውን ተናግረው ነበር፡፡
ከጥናቱ ፀሐፊዎች መካከል አንዱ የሆኑት ዴቪድ ራሰላ “ለበርካታ ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ላላቸው አገራት ውጤቱ ከዓለም አቀፍ ወረርሽኝ አሊያም ከግዙፍ ግጭት ጋር የሚነፃፀር ነው” ብለዋል።
የረድኤት ድጋፉ “ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በተጋላጭ ሕዝቦች ጤና ላይ የታየው እድገት በአፋጣኝ እንዲገታ ወይም ወደነበረበት እንዲመለስ አደጋ ደቅኗል” ሲሉ በባርሴሎና ዓለም አቀፍ ጤና ኢንስቲትዩት ተመራማሪ የሆኑት ዴቪድ ራሰላ አክለው ተናግረዋል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።
ሰኔ 24 ቀን 2017 ዓ.ም
