የኢትዮጵያ ሪፎርም ችግር ያለበት ነዉ በሚል በተደጋጋሚ ይነሳል ነገርግን ብዙዎች እንደ ምሳሌ ሊወስዱት የሚችሉት ነዉ ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡
በኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ቀርበዉ ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሳላቸዉ ጥያቄ ምላሽ እየሰጡ የሚገኙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አይኤምኤፍ እና የአለም ባንክ የኢትዮጵያ ሪፎርም ችግር ያለበት ነዉ በሚል ሪፖርት አቅርበዋል በሚል ብዙ ሲተች ቆይቷል ብለዋል፡፡
ሪፎርሙ በዓለም አቀፍ የፋይናንሻል ኮሚቴ ጭምር የተመሰገነ እና ብዙዎች ምሳሌ ሊያደርጉት የሚችሉት ሪፎርም መሆኑን ግን የአይኤምኤፍ ሪፖርት ያሳያል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ከሪፎርሙ በኋላ በኤክስፖርት ለማግኘት ካቀድነዉ 5.1 ቢሊየን ዶላር ዕቅድ አሁን ላይ 8.1 ቢሊየን ዶላር ማግኘት ችላለች ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ዕቅድ አሳክታ የማታዉቅ አገር ካቀደችዉ በላይ አሳክታለች ብለዋል፡፡
ባለፈዉ ዓመት 8.1 በመቶ ዕድገት ተመዝግቦ ነበር ሲሉ ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ እስከ መስከረም በሚኖረዉ ጊዜ 8.4 በመቶ እና ከዛ በላይ ዕድገት ይመዘገባል ነዉ ያሉት፡፡
በትናንትናዉ ዕለት የአይኤምኤፍ ቦርድ፤ ‹‹ይህ ሪፎርም ወደ ኋላ ካልተመለሰ የኢትዮጵያ ብልጽግና ይረጋገጣል›› የሚል የማረጋገጫ ሪፖርት ሰጥቶናል ብለዋል፡፡
እስካሁን ባለዉ ጊዜ 92 ቢሊየን ብድር መልሰናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ መንግስታቸዉ ወደ ስልጣን ከመጣበት ጊዜ አንስቶ አንድ ዶላር ኮሜርሻል ብድር አለመዉሰዱንም ገልጸዋል፡፡
እስከዳር ግርማ
ሰኔ 26 ቀን 2017 ዓ.ም
