ቴክኖሎጂን በመጠቀም በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ምክንያት በዜጎች ላይ እየደረሰ የሚገኘዉ የስነልቦና እና ግላዊ የማንነት ጥሰቶች ጥቃት እየተበራከተ ስለመምጣቱ ተነግሯል፡፡
በዘርፉ ላይ ጥናት ያደረጉት አቶ ሳሙኤል ልጃገኘሁ፤አሁን ላይ በማህበረሰቡ ላይ እየደረሱ ካሉ ጥቃቶች መካከል የማስፈራሪያ፤የማሸበር፤የስም ማጥፋት፤ጥቃቶች ናቸዉ ብለዋል፡፡
እነዚህ ጥቃቶችም እየደረሱ ያሉት በብዛት ከወንዶች ይልቅ በሴቶች ላይ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
ሌላኛዉ ያነጋገርናቸዉ ጠበቃና የህግ ባለሙያ አቶ ካሳሁን ሙላቱ በበኩላቸዉ፤በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በኩል እየደረሱ ያሉት ጥቃቶቹ ኮንፒተር እና የእጅ ስልኮችን በመጠቀም መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
አቶ ካሳሁን የስነልቦና እና የግለሰብ መብት ጥሰት ከትላልቅ ድርጅቶች ጀምሮ እስከ ግለሰቦች ድረስ ይደርሳል ያሉ ሲሆን፤በዚህም ሰዎች በሚደርስባቸዉ ተጽእኖ ምክንያት እስከሞት የሚደርሱ ስለመኖራቸዉ ነግረዉናል፡፡
የህግ ባለሞያው አቶ ካሳሁን እንዲህ አይነቱን የህግ ጥሰት ለመዳኘት የወጣ የህግ ማእቀፍ በብዛት ቢኖርም ተግባራዊነቱ ላይ ችግር አለ ብለዋል፡፡
በህብረተሰቡም በኩል ጉዳዩን ወደ ህግ መውሰድ ላይ የግንዛቤ ችግር አለ ያሉት የህግ ባለሞያው ህብረተሰቡ እንዲህ አይት ጥቃት ሲደርስበትም ሆነ ሲመለከት ወንጀል እየተሰራበት መሆኑን አውቆ ለህግ ማመልከት እንዳለበት ገልፀዋል።
ድርጊቱን እየፈጸሙ ያሉ ግለሰቦችም በህግ እንደሚያስጠይቅ አውቀው ከእንዲህ አይነት ተግባር እንዲታቀቡ አቶ ካሳሁን ሞያው ምክራቸውን ለግሰዋል ፡፡
ልኡል ወልዴ
ሐምሌ 4 ቀን 2017 ዓ.ም
