የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ፤ ከተደራጀ የወንጀል ድርጊት ጋር ግንኙነት አላቸው የሚል ውንጀላ የቀረበባቸውን የአገሪቱን የፖሊስ ሚኒስትር ሴንዞ ሙቹኑን በአስቸኳይ “እረፍት” አስወጡ።
ራማፎሳ፤ እሁድ ዕለት በቴሌቪዥን ቀጥታ በተላለፈ እና ለአገሪቱ ዜጎች ባደረጉት ንግግር፤ ክሶቹን ሕገ መንግሥቱን የሚያዳክሙ እና ብሔራዊ ደህንነትን አደጋ ላይ የሚጥሉ ሲሉ የገለጿቸው ሲሆን ጉዳዩ በፍትህ ኮሚሽን እንደሚታይ አስታውቀዋል።
የሕግ ፕሮፌሰር የሆኑ ፊሮዝ ካቻሊያ ጊዜያዊ የፖሊስ ሚኒስትር ሆነው መሾማቸውንም ይፋ አድርገዋል።
ሙቹኑ በበኩላቸው ምንም ዓይነት ጥፋት አለመፈጸማቸውን በመግለጽ “ለቀረቡባቸው ክሶች ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ ነኝ” ብለዋል።
በሙቹኑ ላይ ከቀረቡት ክሶች መካከል የፖለቲካዊ ግድያዎች በተመለከቱ ምርመራዎች ውስጥ ጣልቃ መግባትን እና ከሕግ አስፈጻሚ ኤጀንሲዎች ጋር የተያያዙ የሙስና ድርጊቶች ይገኙበታል።
ፕሬዚዳንቱ በትናንቱ ንግግራቸው፤ በሙቹኑ ላይ የቀረቡት ክሶች “አስቸኳይ እና አጠቃላይ ምርመራን እንዲደረግ” ጥሪ አቅርበዋል።
በአገሪቱ ምክትል ዋና ዳኛ የሚመራው የፍትህ ኮሚሽን ሁሉንም ውንጀላዎች እንደሚመረምር ተናግረዋል።
ሐምሌ 7 ቀን 2017 ዓ.ም
