በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኣሪ ዞን በደቡብ ኣሪ ወረዳ ኮመር ቀበሌ ውልሽር በሚባል አካባቢ ትናንት ምሽት 4:00 ገደማ በተከሰተ የመሬት መንሸራተት አደጋ ከአንድ ቤተሰብ የአምስት ሰዎች ሕይወት ተቀጥፏል፡፡
በመሬት መንሸራተት አደጋው ሰለባ የሆኑት አባትና እናት ከ3 ልጆቻቸዉ ጋር መሆኑንም ሰምተናል።
ከዚህም በተጨማሪ በአደጋዉ 3 የመኖሪያ ቤቶች ከቤት እንስሳት ጋር በአደጋው ሰጥመዋል ።
በኢትዮጵያ ደቡባዊ ክፍል በተደጋጋሚ የመሬት መንሸራተትና ሌሎች የተፈጥሮ አደጋዎች እየተከሰቱ መሆናቸው የሚታወቅ ነዉ።
ከተፈጥሮ አደጋዎች ጋር ተያይዞ በክልሉ ዳሰነች ወረዳ በቱርካና ሀይቅ ሙላትና መስፋፋት ምክንያት የዳሰነች ወረዳ ዋና ከተማ የሆነዉ ኦሞራቴ ስጋት እንደሆነ ጣቢያችን መዘገቡ የሚታወስ ነዉ።
የወረዳዉ 66 በመቶ መሬት እንዲሁም በርካታ ቀበሌዎች በዉሃ ሙላት መጥለቅለቃቸዉም እየተገለፀ ነው።
ወቅቱ ክረምት እንደመሆኑ በሌሎች የክልሉ አካባቢዎችም ተመሳሳይ አደጋ እንዳይከሰት የስጋት ቦታዎች ላይ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የጨንቻ ዙሪያ ወረዳ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት አስታውቋል።
ሀምሌ 15 ቀን 2016 በክልሉ ለብዙዎች ህይወት ማለፍ ምክንያት የሆነዉ የመሬት መንሸራተት ማጋጠሙ ይታወሳል።
ሀኒፍ ሀምዛ
ሀምሌ 14/2017 ዓ.ም
