ሳዑዲ አረቢያ የፍልስጤም መንግስት እስካልተመሰረተ እና በጋዛ ያለው ጦርነት እስካላበቃ ድረስ ከእስራኤል ጋር መደበኛ ግንኙነት አትጀምርም ሲሉ የሳዑዲ አረብያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ልዑል ፋይሰል ቢን ፋርሃን ተናግረዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የእስራኤል የዘር ማጥፋት ወንጀል በጋዛ እየቀጠለ ባለበት ሁኔታ ከእስራኤል ጋር ስለ መደበኛ ግንኙነት መነጋገር እንደማይቻል አጽንኦት ሰጥተዋል።
በጋዛ ያለው ግጭት ካበቃ እና የጋዛ ህዝብ ስቃይ ከተቃለለ ብቻ ለዉይይት ክፍት ልንሆን እንችላለን ብለዋል፡፡
በጋዛ የማያቋርጥ ሞት፣ስቃይ እና ውድመት ባለበት ሁኔታ ስለ ግንኙነት ውይይት ለማድረግ ምንም ምክንያት ወይም ተዓማኒነት የለም ሲሉ ተደምጠዋል።
ቀደም ሲል ልዑል ፋይሰል፤ የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በቅርቡ የፍልስጤምን መንግስት በይፋ እውቅና ለመስጠት ያደረጉትን ቃልኪዳን እንደሚቀበሉ ተናግረዋል።
እስካሁን ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት 1መቶ93 አባል ሀገራት ውስጥ 1መቶ49 ሀገራት ፍልስጤምን እውቅና የሰጡ ሲሆን፤ ይህ ቁጥር እስራኤል በጥቅምት 2023 በጋዛ ላይ ጦርነት ከጀመረችበት ጊዜ ጀምሮ በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል ሲል ሚድል ኢስት ሞኒተር ዘግቧል።
ሀኒፍ ሀምዛ
ሐምሌ 22/2017 ዓ.ም
