በመላዉ ሃገሪቱ ያሉ17 የቅርንጫፍ ዋና መስሪያ ቤቶች እያንዳዳቸዉ 2ሺህ ችግኞችን እንዲተክሉ መመሪያ መሰጠቱን የኦሮሚያ ህብረት ስራ ባንክ አስታወቀ

በአንድ ጀምበር 700 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል በተያዘው የዛሬው ዕለት መርሐግብር ላይ የኦሮሚያ ህብረት ስራ ባንክ በመላዉ ሃገሪቱ ያሉት 17 የቅርንጫፍ ዋና መስሪያ ቤቶች እያንዳንዳቸዉ 2ሺህ ችግኞችን እንዲተክሉ መመሪያ መሰጠቱን አስታዉቋል፡፡

የባንኩ ስራ አስፈፃሚ አቶ ደርበው አስፋው፣በከተማዋ ላለፉት ዓመታት በተከናወነው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በርካታ ለዉጦችን አይተናል ያሉ ሲሆን፣ ዘንድሮም ለምግብነት፣ ለኢንዱስትሪ ግብዓት፣ ለከተማ ውበትና ለሌሎችም አገልግሎቶች የሚውሉ ችግኞችን እየተከልን እንገኛለን ብለዋል፡፡

በየዓመቱ መትከል ብቻ ሳይሆን በምን መልኩ መከታተል ይቻላል የሚለዉን በግምት ዉስጥ በማስገባት ዉይይት መደረጉን እንዲሁም በገንዘብ ለመደግፍ መታሰቡንም ባንኩ ገልጿል፡፡

ባንኩ በሃገሪቱ አጠቃላይ 7መቶ 45 ቅርንጫፎች እና 17 የቅርንጫፍ ዋና መስሪያ ቤቶች እንዳሉት ስራ አስፈጻሚዉ ተናግረዋል፡፡

አቶ ደርቤ በአዲስ አበባ ዉስጥ እና ዙሪያዋ ያሉ የባንኩ ሰራተኞች በአረንጓዴ አሻራ መረሃግብር ላይ እየተሳተፉ መሆኑን ገልጸዉ፤እንደ ዋና መስሪያ ቤት 6 ሺህ ችግኞችን ለመትከል አቅደናል ሲሉም ገልጸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር ) ዛሬ ማለዳ በአንድ ጀምበር 700 ሚሊዮን ችግኞችን የመትከል መርሐ-ግብር በይፋ ማስጀመራቸዉ ይታወቃል፡፡

ልኡል ወልዴ

ሐምሌ 24/2017 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *