በሱዳን ዳርፉር ግዛት በኮሌራ 80 ሰዎች ህይወታቸዉ ማለፉ ተገለጸ

በበሽታዉ ከ2 ሺህ 1መቶ በላይ ሰዎች ተጠቅተዋል ተብሏል፡፡

በተባበሩት መንግስታት የህፃናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) እንዳስታወቀው፤ በሱዳን አምስቱ የዳርፉር ግዛቶች እስከ ሀምሌ 30 ድረስ ቢያንስ 80 ሰዎች በኮሌራ ህይወታቸውን ያጡ ሲሆን፤ ከ2 ሺህ 1መቶ በላይ ሰዎች ደግሞ በበሽታው ተይዘዋል፡፡

ዩኒሴፍ ባወጣው መግለጫ፤ከሰኔ 21 ጀምሮ በሰሜን ዳርፉር ግዛት በታዊላ ከተማ ብቻ 20 ሰዎች በወረርሽኙ ህይወታቸውን ያጡ ሲሆን፤ከ 1 ሺህ በላይ ሰዎች ደግሞ በበሽታው መያዛቸውን ገልጿል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሰሜን ዳርፉር ከ6መቶ40 ሺህ በላይ ህጻናት ለጥቃት፣ ለረሃብ እና ለኮሌራ የተጋለጡ መሆናቸውን አስጠንቅቋል።

የዩኒሴፍ የሱዳን ተወካይ ‹‹ህመሙ ምንም እንኳን መከላከል የሚቻል እና በቀላሉ ሊታከም የሚችል ቢሆንም፤ ኮሌራ በታዊላ እና በሌሎች የዳርፉር አካባቢዎች በፍጥነት በመዛመት የህጻናትን በተለይም የትንንሾችን እና በጣም ተጋላጭ የሆኑትን ህይወት አደጋ ላይ እየጣለ ነው››ብለዋል።

እነዚህን እርዳታ የሚሹ ህጻናት ለመድረስ ደህንነቱ የተጠበቀና ያልተገደበ ተደራሽነት እንዲኖር እጠይቃለሁ፤ልጆቹ አንድ ቀንም መጠበቅ አይችሉም ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የተባበሩት መንግስታት አሃዛዊ መረጃ እንደሚያሳየው ከነሀሴ 2024 ጀምሮ ከሱዳን 18 ግዛቶች ውስጥ በ17ቱ ከ94 ሺህ በላይ የኮሌራ ተጠቂዎች የተገኙ ሲሆን፤ከ2 ሺህ 3መቶ በላይ ሰዎች ደግሞ መሞታቸው ተዘግቧል።

ሱዳን ከሚያዝያ 2023 ጀምሮ በጦሩ እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መካከል በተፈጠረ ውጊያ ስትታመስ ቆይታለች።

በተባበሩት መንግስታት እና በአካባቢው ባለስልጣናት መረጃ መሠረት ግጭቱ ከ20 ሺህ በላይ ሰዎችን የገደለ ሲሆን፤ 14 ሚሊዮን ሰዎችን አፈናቅሏል።

ይሁን እንጂ የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ጥናት የሟቾችን ቁጥር ወደ 1መቶ30 ሺህ ገደማ ያደርሰዋል ሲል የዘገበዉ አናዶሉ ነዉ።

እስከዳር ግርማ

ሐምሌ 28/2017 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *