የአፍዴራ ከተማም የመሬት መንቀጥቀጥ ስንጥቆች እየታየበት መሆኑን ጣቢያችን ሰምቷል ።
የሰመራ ዩኒቨርስቲ አደጋዉን በተመለከተ በስነምድር ባለሙያዎቹ ጥናት እና ምልከታ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጿል።
በሰመራ ዩንቨርስቲ የስነምድር ባለሙያ የሆኑት መሀመድ አሊ ከጣቢያችን ጋር በነበራቸዉ ቆይታ የመሬት ስንጥቁ ከሳምንታት በፊት ተከስቶ በነበረዉ የኤርታሌ እሳተ ጎመራ ፍንዳታ ምክንያት መፈጠሩን ነግረዉናል።
ባለሙያዉ የአፍዴራ ከተማ ላይ የሚታየዉ የመሬት መንቀጥቀጥ በፈጠረዉ መሬት መሰንጠቅ ምክንያት ጎድጓዶች እየተፈጠሩ መሆኑን አንስተዋል።
በሌላ በኩል በአፍዴራ የጨዉ ባህር አካባቢ በሚታየው ስንጥቅ ዉሃዉ ከስር ወደ ላይ የመዉጣት ባህሪ አካባቢዉ ላይ መታየቱን ባለሙያዉ ለኢትዮ ኤፍ ኤም ተናግረዋል።
የሰመራ ዩንቨርስቲ ስነምድር መምህሩ እየተፈጠረ ያለዉ ክስተት ከባለፈዉ ዓመት ጀምሮ ከአዋሽ ፈንታሌ ከተፈጠረው ክስተት ጋር ተያያዥነት ያለዉ እንደሆነ ይገመታል ብለዋል።
አካባቢዉ ለእንደዚህ አይነት ክስተት ተገማች ቢሆንም ከሳምንታት በፊት የተፈጠዉ የእሳተ ጎመራ ከ10 አመታት በፊት ክስተቱ ተፈጥሮባቸዉ የተደፈኑ መሬቶች ላይ በድጋሜ የተፈጠሩ መሆኑን ጠቁመዋል።
ሆኖም ከሳምንታት በፊት የተፈጠረዉ የእሳተ ጎመራ ክስተት እስከዛሬ ከምናቀዉ የተለየ መሆኑን ነዉ መረዳት የቻልነዉ ሲሉ አቶ መሀመድ ተናግረዋል።
እየተፈጠረ ያለዉን ተፈጥሮአዊ ክስተት መሠረት ያደረገ እና ወዴት እያመራ ነዉ የሚለዉን መመለስ የሚችል ሰፊ ጥናት እና ክትትል እንደሚያስፈልግ ተገልጿል።
በአካባቢው ያለዉ ማህበረሰብ ስለ ክስተቱ ያለዉ መረዳት ያነሰ በመሆኑ እራሱን እንዴት መከላከል እንዳለበት አያዉቅም ያሉት ባለሙያዉ በሰዉ ላይ ሊደርስ የሚችልን አደጋ መቀነስ የሚቻለዉ ግንዛቤዉን በመስጠት እንደሆነ አስታውሰዋል።
ሰመራ ዩኒቨርሲቲ አደጋውን ለመገምገም እና ለመከላከል የሚያስችሉ ጥረቶችን ለመደገፍ፣ ሀገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ የጂኦ ሳይንሳዊ ባለሙያዎች በአስቸኳይ በመስክ ምርምርና ክትትል ላይ እንዲተባበሩ ጥሪ ማቅረቡ የሚታወስ ነዉ።
ቁምነገር አየለ
ሐምሌ 28/2017 ዓ.ም
