የዴንማርክ መካነ አራዊት እንስሳቱን ለመመገብ የማይፈለጉ የቤት እንስሳትን ማህበረሰቡ እንዲለግሰዉ ጠይቋል

በዴንማርክ የሚገኝ አንድ መካነ አራዊት አዳኝ እንስሳቱን ለመመገብ በሚያደርገው ጥረት፤ህብረተሰቡ የማይፈልጓቸዉን ጤናማ የቤት እንስሳቶቻቸውን እንዲለግሱት ጥሪ አቅርቧል።

የአልቦርግ መካነ አራዊት በሰለጠኑ ሰራተኞቼ ‹‹በርህራሄ ይገደላሉ›› ያላቸውን በህይወት ያሉ ዶሮዎችን፣ ጥንቸሎችን እና አሳማዎችን እንዲለግሱት ጠይቋል።

መካነ አራዊቱ በህይወት ያሉ ፈረሶችንም እንደ ልገሳ እቀበላለሁ፤ባለቤቶቹም ከቀረጥ ቅናሽ ተጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ ብሏል።

መካነ አራዊቱ በኢንስታግራም ገፁ ‹‹የእንስሳትን ተፈጥሯዊ የምግብ ሰንሰለት የመከተል ሃላፊነት አለብን፤ ስለዚህ ትናንሽ እንስሳት ደግሞ ለአዳኞቻችን የአመጋገብ ስርዓት አስፈላጊ አካል ናቸው›› ሲል አስረድቷል።

መካነ አራዊቱ በገለጸዉ መሰረት ፤ ትናንሽ እንስሳት በሳምንቱ ቀናት ሊለገሱ የሚችሉ ሲሆን፤ ያለ ቀጠሮ ከሆነ በአንድ ጊዜ ከአራት የማይበልጡ እንስሳት ብቻ መሆን አለባቸው።

መካነ አራዊቱ ፈረሶችን ለመለገስ የሚያስፈልጉትን ቅድመ ሁኔታዎችም ማስቀመጡን ነዉ የገለጸዉ፡፡

ከመስፈርቶቹም መሃከል የፈረስ ፓስፖርት ያላቸዉ እንዲሁም ባለፉት 30 ቀናት ከህመም ነጻ ሆነዉ የቆዩ መሆን አለባቸዉ የሚል ይገኝበታል፡፡

በዚህም እንስሳቶቻቸውን በማስረከብ ከተሳካላቸው የፈረስ ለጋሾች የቀረጥ ቅናሽ ሊያገኙ ይችላሉ ብሏል።

የመካነ አራዊቱ ምክትል ዳይሬክተር በሰጡት መግለጫ፤ የመካነ አራዊቱ ስጋ ተመጋቢዎች ለብዙ አመታት ትናንሽ እንስሳትን ሲመገቡ ቆይተዋል ብለዋል።

ስጋ ተመጋቢዎችን ስንንከባከብ ስጋ፣ በተለይም አጥንት ያለበትን ምግብ በመስጠት በተቻለ መጠን ተፈጥሯዊ ምግባቸውን እንዲያገኙ ማድረግ አስፈላጊ ነው ሲሉ አስረድተዋል።

ስለሆነም በተለያዩ ምክንያቶች ህይወታቸዉ የሚያልፉ እንስሳትን በዚህ መንገድ ጥቅም ላይ እንዲውሉ መፍቀድ ምክንያታዊ ነው ብለዋል።

በዴንማርክ ይህ አሰራር የተለመደ ነዉ፤ ብዙ አጋሮቻችን አስተዋፅኦ የማድረግ እድሉን ይጠቀሙበታል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

እንደ ልገሳ የምንቀበላቸው እንስሳት ዶሮዎች፣ ጥንቸሎች፣ አሳማዎች እና ፈረሶች ናቸው ይታወቅልን ብለዋል፡፡

በመካነ አራዊቱ ውስጥ ከሚገኙ አዳኞች መካከል አንበሶች እና ነብሮች ይገኙበታል ሲል የዘገበዉ ቢቢሲ ነዉ።

እስከዳር ግርማ

ሐምሌ 29/2017 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *