ለሽግግር ፍትህ ሂደት ከሕግ ረቂቅ ሰነዶች ዉጪ ሌሎች ተግባራት በታቀደላቸው ጊዜ አለመከናወናቸው አሳሳቢ ነው ተባለ።
በኢትዮጵያ የሽግግር ፍትሕ ሂደትን የሚመራ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ በሚያዝያ ወር 2016 ዓ.ም. በሚኒስትሮች ምክር ቤት መፅደቁ የሚታወስ ነዉ።
ጉዳዩ ዙሪያ በፍትሕ ሚኒስቴር እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች ÷ አጠቃላይ ሂደቱ እየተመራ ያለበት አግባብ ለሕዝብ ግልጽ አለመደረጉም ተገልፆል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮምሽን ባወጣዉ ሪፖርት ላይ ነዉ ይህ የተገለፀዉ።
ኮምሽኑ በሪፖርቱ እንደገለፀዉ የሽግግር ፍትሕን የመተግበር የፖለቲካ ቁርጠኝነት በሀገሪቱ ያሉ ግጭቶችን የማስቆም ጥረቶችን ሊያካትት ይገባል ብሏል።
ለሽግግር ፍትህ ትግበራ ለ ግጭቶች እና የጸጥታ ችግሮች ምላሽ ለመስጠት እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች ውጤታማ አለመሆን አሳሳቢ ተግዳሮት ሆኗል ሲል አስቀምጧል።
የሽግግር ፍትሕ መተግበሪያ ረቂቀ ሕጎች ለሕዝብ ውይይት ይፋ አለመደረጋቸው ኮምሽኑ ጠቅሷል።
በተለይም የሽግግር ፍትሕ ሂደቱ ወደ ትግበራ ምዕራፍ ከተሸጋገረ በኋላ የመቀዛቀዝ አዝማሚያ እያሳየ መሆኑ አሳሳቢ ጉዳይ ነዉ ተብሏል።
በኢትዮጵያ ባለፉት 30 ዓመታት ለተፈፀሙ እና አሁን እየተፈፀሙ ላሉ የጦርነት ፣ የማፈናቀል እና ሌሎች በደሎች አጥፊዎችን በህግ ፊት ለማቆም፣ ተጎጂዎችንም ለመካስ የሽግግር ፍትህ መፍትሄ ተደርጎ እንደቀረበ ይታወሳል።
ቁምነገር አየለ
ነሐሴ 6/2017 ዓ.ም
