የእስራኤል ካቢኔ ሐሙስ ዕለት ባደረገው ስብሰባ የጋዛ ከተማን የመያዝ እቅድ ማጽደቁን የመከላከያ ሚኒስትሩ እስራኤል ካትዝ አርብ ዕለት አስታውቀዋል።
ሃማስ “ጦርነቱን ለማቆም እስራኤል ያስቀመጠችውን ቅድመ ሁኔታ በዋናነት ሁሉንም ታጋቾች መልቀቅ እና ትጥቅ መፍታት” ካልተቀበለ “የገሃነም በሮች በሃማስ ላይ ይከፈታሉ” ብለዋል ካትዝ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በግብፅና በኳታር የቀረበውን የተኩስ አቁም ስምምነት እንደማይቀበሉ ተናግረው፤ “ለእስራኤል ተቀባይነት ባለው መልኩ” የቀሩ ታጋቾች በሙሉ እንዲለቀቁ እና የጋዛ ጦርነት እንዲቋጭ የሚያስችል ድርድር እንዲጀመር መመሪያ ሰጥተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ካቢያኔያቸው ዓለም አቀፍ እና የአገር ውስጥ ተቃውሞ የገጠመውን የጋዛ ከተማን ወረራ ማጽደቁን ሐሙስ ምሽት ለወታደሮቻቸው ተናግረዋል።
ሐማስ በኳታር እና በግብጽ አሸማጋይነት የቀረበውን ለ60 ቀናት የሚቆይ የተኩስ አቁም ስምምነት ሰኞ ዕለት መቀበሉን አስታውቋል። ይህ ስምምነት በጋዛ ከቀሩት ታጋቾች ግማሾቹን እንዲለቀቁ የሚያስችል ነው።
ኔታንያሁ ይህንን ሐማስ የተቀበለውን ስምምነት እንዳልተቀበሉት በይፋ ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጋዛን ወረራ በበላይነት የሚያየውን በእስራኤል የሚገኘውን ዋና መስሪያ ቤት ሐሙስ ምሽት በጎበኙበት ዕለት “ሁሉንም ታጋቾቻችንን ለማስለቀቅ ድርድር በአስቸኳይ እንዲጀመር መመሪያ ሰጥቻለሁ” ብለዋል።
አክለውም “የእስራኤል መከላከያ ሰራዊት የጋዛ ከተማን እንዲቆጣጠር [እንዲወር] እና ሐማስን እንዲያሸንፍ የወጣውን ዕቅድ አጽድቄያለሁ ለማለት ነው የመጣሁት” ሲሉ ተናግረዋል።
የፍልስጤሙ ሃማስ ቡድን ሰኞ ዕለት የግብፅ እና የኳታር አስታራቂዎች ያቀረቡትን የጋዛ የተኩስ አቁም ጥያቄ በዝርዝር ሳያስረዳ መቀበሉን አስታውቋል ሲል አናዶሉ በዘገባው አስነብቧል።
ሀኒፍ ሀምዛ
ነሐሴ 16 /2017 ዓ.ም
