በኢትዮጵያ በተለያዩ ህብረት ስራ ማህበራት ውስጥ በጠቅላላው 25 ሚሊዮን የሚጠጉት ዜጎች በንቃት እንደሚሳተፉ የኢትዮጵያ ህብረት ስራ ኮምሽን የፋይናንስ ህብረት አስታውቋል።
በኢትዮጵያ ህብረት ስራ ኮምሽን የፋይናንስ ህብረት ስራ ልማት መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ብርሃኑ ዱፌራ፤ህብረት ስራ ማህበራት አላማቸው ግለቦች በተናጠል ማሳካትና መፈታት ያልቻሉትን ችግር በጋራ እንዲፈቱ ማስቻል ነው ብለዋል።
አቶ ብርሃኑ ከመሰረታዊ እስከ ፌድሬሽን ድረስ በዓለም ገበያም በሃገር ውስጥም ብዛት ያላቸው ትላልቅ ህብረት ስራ ማህበራት አሉ ሲሉም ተናግረዋል።
ከዚህ ውስጥ የቁጠባና ብድር ህብረት ስራ ማህበራት ወደ 8.2 ሚሊዮን የሚጠጉ አባላት በመደበኛነት የሚቆጥቡና በቆጠቡት ልክ ብድር የሚወስዱ መሆናቸውንም ገልፀዋል።
በተለይ የከተማ ህብረት ስራ ማህበራት በከተማዋ ውስጥ ያለውን መሰረታዊ የፍጆታ ምርቶችን እጥረት በማረጋጋትና ምርቶችን ከገበሬዎች በመግዛት ለማህበረሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረቡ ይገኛሉ ነው ያሉት።
ከፍጆታ ምርቶች ባሻገርም ህብረት ስራ ማህበራት ለማህበረሰቡ አማራጭ የፋይናንስ ምንጭ በመሆን ፣የስራ እድል በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያደረገ ይገኛል ሲሉም አስረድተዋል።
ዋና ስራ አስፈፃሚው ይህን ያሉት አሚጎስ የገንዘብ ቁጠባ እና ብድር ህብረት ስራ ማህበር በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የመጀመሪያውን ቅርንጫፍ በአዳማ ከተማ መክፈቱን በገለፀበት መድረክ ነው።
የአሚጎስ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ፍጹም አብርሃ፤ ማህበሩ የተለያዩ የብድር አማራጮችን በማቅረብ በትራንስፖርት፣ በማኑፋክቸሪንግ እና በሌሎች የስራ ዘርፎች እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
አቶ ፍፁም፥ ለአባላቶቻችን በአነስተኛ ቁጠባ እና በአነስተኛ ወለድ የቤት፣የመኪና እና የንግድ ማስፋፊያ የገንዘብ ብድር እያቀረብን እንገኛለንም ብለዋል::
ማህበሩ በቀጣይ በጅማ እና ሌሎችም ከተሞች በቅደም ተከተል የማስፋት ስራ ይሰራል ተብሏል::
በመጨረሻም ማህበራቱ ለተቋቋሙበት አላማ እየሰሩ መሆኑን እና ችግር ሲፈጠር እርማት የሚሰጥበት ህግና መመሪያ መውጣቱም ተነግሯል።
ልኡል ወልዴ
መስከረም 12/2018 ዓ.ም
