ቦትስዋና በ2024 የፓሪስ ኦሎምፒክ በ200 ሜትር ሌስሊ ቶቤጎ ለሀገሪቱ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካም ጭምር በርቀቱ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳልያ በማምጣት ታሪክ ሰራ።
ለዚህ ክብሩ ሲባልም በቅርቡ ከሀገሪቱ የመገበያያ ገንዘብ (ፑላ ይባላል) መካከል በ50 ፑላ ኖት ላይ ምስሉ ታትሞ ለመገበያያነት እንዲውል ተደርጓል።
እሁድ ዕለት ፍፃሜውን ባገኘው የቶኪዮ የዓለም ሻምፒዮና ላይ ደግሞ ቦትስዋና በ4×400 የወንዶች የፍፃሜ ውድድር በድጋሚ ለራሷና ለአፍሪካም የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳልያ በመውሰድ ታሪክ መስራቷን ቀጥላለች።
ውድድሩ ሲካሄድ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ዱማ ቦኮ በተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ለመታደም በአሜሪካ ኒውዮርክ ነበር የሚገኙት።
ከድሉ በኋላ በልጆቻቸው ስኬት መላ አፍሪካውያን ኩራት እንደተሰማቸው የገለፁት ፕሬዝዳንት ቦኮ “የእኛ አልማዝ 💎 ከምድር በታች ያለው ሳይሆን የዓለም ሻምፒዮን የሆኑት ጀግኖች ልጆቻችን ናቸው አልማዞቻችን። በመሆኑም ሴፕቴምበር 30 የነፃነት ቀናችን ሲሆን ከዛ አንድ ቀን ቀደም ብሎ ያለው ሴፕቴምበር 29 ደግሞ ከዘንድሮ ጀምሮ ለጀግኖቻችን ክብር ሲባል በየዓመቱ ህዝባዊ በዓል ሆኖ እንዲከበር መንግስታችን ወስኗል” ብለዋል።
ምስጋናው ታደሰ
መስከረም 14/2018 ዓ.ም
