የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት በሳርኮዚ እስር ምክንያት በዳኞች ላይ እየደረሰ ያለውን የሞት ዛቻ አወገዙ

የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን፤ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ሳርኮዚ እስር ከተፈረደባቸዉ በኋላ በዳኞች ላይ እየደረሰ ያለውን የሞት ዛቻ አውግዘዋል።

ማክሮን በበርካታ ዳኞች ላይ የደረሰው ድሮም ሆነ በቅርቡ የተፈፀመ ጥቃት እና የሞት ዛቻ ተቀባይነት የለውም፤ ለዚህም ነው የፍትህ ሚኒስትሩን እና የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩን በአስቸኳይ ጠርቼ ወንጀለኞችን ለይተው ለፍርድ እንዲያቀርቡ ያዘዝኩት ሲሉ በማህበራዊ ገጻቸዉ ላይ ጽፈዋል፡፡

የህግ የበላይነት የፈረንሳይ ዲሞክራሲ መሰረት መሆኑን አጽንኦት የሰጡት ፕሬዝዳንቱ፤ የፍትህ አካላት ነጻነት፣ ገለልተኝነት እና የዳኞች ጥበቃ አስፈላጊ ምሰሶዎች መሆናቸውን ጠቁመዋል።

የፍርድ ቤት ውሳኔዎች በህዝባዊ ክርክር አስተያየት ሊሰጥባቸው ወይም ሊተቹ ይችላሉ ግን ሁልጊዜም የሁሉንም ሰው ክብር በጠበቀ መልኩ መሆን አለበት ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ይግባኝ የማቅረብ መብትን በመጠቀም መከራከር ይቻላል ሲሉም አክለዋል።

የማክሮን መግለጫ የፓሪስ አቃቤ ህግ ቢሮ ፤ ዓርብ ዕለት በሳርኮዚ እስር ምክንያት የፍርድ ቤቱ ፕሬዝዳንት ላይ እየደረሱ ካሉ የዛቻ መልዕክቶች ጋር በተያያዘ ሁለት የተለያዩ ምርመራዎች መጀመራቸውን ካስታወቀ በኋላ መሆኑ ተዘግቧል፡፡

የቀድሞው የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ሳርኮዚ፤ በ2007 የምርጫ ዘመቻቸው ወቅት ከሊቢያ የገንዘብ ድጋፍ አግኝተዋል በሚል ክስ የአምስት አመት እስራት ተፈርዶባቸዋል እንደ አናዶሉ ዘገባ።

እስከዳር ግርማ

መስከረም 19/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *