ሆስፒታሉ ከዚህ በፊት ከነበረበት ችግር በተወሰነ መልኩ መሻሻሎች እንዳሉት እና የእናቶች ወሊድ ህክምናን በአግባቡ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል አቋም ላይ መሆኑን የሆስፒታሉ ክሊኒካል ዳይሬክተር ዶ/ር አብረሃ ገ/እግዚአብሔር ለኢትዮ ኤፍኤም ተናግረዋል፡፡
ባሳለፍነው ሳምንት የተቋሙ የልብ ህክምና አገልግሎት፤ ከጣሊያን በመጡ ባለሙያዎች ታግዞ 11 ህሙማን የልብ ድጋፍ ሰጪ ባትሪዎች እንዲያገኙ ማድረጉን ገልፀዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ከአገልግሎት ውጪ የነበሩ የህክምና መሳሪያዎች በጣልያን ባለሙያዎች ድጋፍ ወደ ስራ መመለሳቸውን ጠቅሰዋል፡፡
ይሁን እንጂ አሁንም የህክምና አገልግሎት መስጫ መሣሪያዎች ላይ ተደጋጋሚ ብልሽት፣ የተወሰኑ መድሃኒቶችና የመገልገያ ዕቃዎች አቅርቦት ችግር መኖሩን ዶ/ር አብረሃ አንስተዋል፡፡
እንዲሁም የአንቡላንስ አገልግሎት በበቂ ሁኔታ እየተሰጠ አይደለም ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ከዚህ በፊት የነበረው የሰራተኞች የ17 ወራት ደሞዝ አሁንም እንዳልተከፈለ አስታውሰዋል፡፡
የአገልግሎቶችን ጥራት ለማሻሻልና ለባለሙያዎች ምቹ የስራ አካባቢ እንዲኖር ለማስቻል ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀራርበው እንደሚሰሩም ዶ/ር አብረሃ ተናግረዋል፡፡
ሐመረ ፍሬው
መስከረም 26/2018 ዓ.ም
