በተያዘው በ2018 ዓመት አዲሱ የተሽከርካሪዎች መለያ የሰሌዳ ቁጥር ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ይደረጋል ተባለ ፡፡
በኢትዮጽያ ለ23 ዓመታት ጥቅም ላይ ሲውል የቆየው የተሽከርካሪዎች ሰሌዳ ከሁለት ወር በኋላ በአዲሱ ሰሌዳ ወይም ታርጋ ቅየራ መደረግ እንደሚጀመር እና በተያዘው አመት ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ እንደሚሆን ተገልጿል።
የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ሚንስትር ዶ/ር አለሙ ሲሜ፤የተሽከርካሪዎቹ የመለያ ቁጥሩ ለውጥ ማድረግ ያስፈለገው ነባሩ የሰሌዳ አይነትና ምልክቶች፣ አመራረት፣ አሰረጫጨትና አወጋገድ ወቅቱ ከሚጠይቀዉ ተጨባጭ ሁኔታና ከዘርፉ ዕድገት ጋር ያልተጣጣመ በመሆኑ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ተቀብላ ያፀደቀቻቸውን ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ያካተተ አለመሆኑ፣ ወደፊት አለም ከሚደርስበት የመንገድ ትራንስፖርት አገልግሎትና ዕድገት አንጻር አብሮ የሚሄድ ባለመሆኑ ለውጥ ተደርጓል ሲሉ ተናግረዋል።
በተጨማሪም የአገልግሎት አሰጣጡ ምልልስ የበዛበት፣ ሀብትንና ጊዜን ሲያባክን የነበረ፣ ለሙስናና መልካም አስተዳደር ችግሮች ያጋለጠ፣ የማምረትና የማሰራጨት ሰንስለቱ ለቁጥጥር አመቺ አለመሆኑ፣ ተመሳሳይ መለያ ቁጥሮች በሀገራችን መበራከት ሌላኛው ምክንያት ነው ብለዋል።
የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ በርዖ ሃሰን በበኩላቸው፤ቀደሚሲል የነበረው የሰሌዳ ቁጥጥር አሰጣጥ ለ9 ሚሊዮን አሽከርካሪዎች ብቻ ይሰጥ የነበረ ሲሆን አዲሱ ለ1መቶ21 ሚሊዮን ተሽከርካሪዎች መስጠት የሚያስችል ነው ሲሉ አስረድተዋል።
ሆኖም አዲሱን የሰሌዳ ቁጥር የሚያስቀይሩት የአሽከርካሪ ባለቤቶች ታርጋውን እንደ አዲስ ሳይሆን የማስቀየሪያው ብቻ ይከፍላሉ ብለዋል።
በኢትዮጽያ ለመጨረሻ ጊዜ በ1994 ዓ.ም የሰሌዳ ቅየራ የተደረገ መሆኑና በሀገሪቱ የተመዘገቡ የተሽከርካሪዎች ቁጥር 1.6 ሚሊዮን በላይ መሆኑን ተጠቅሷል፡፡
ሆኖም ሁሉም የክልልና ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ቢሮዎች፣ የህግ አስከባሪ አካላት በተለይም የተሽከርካሪ ባለቤቶች የተሽከርካሪውን ህጋዊ ሰነድ በማዘጋጀት በሚወጣው ስሌዳ መሰረት የተሽከርካሪውን የቴክኒክ ምርመራ በማረጋገጥ ለአፈጻጸሙ አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ የሚል ጥሪ ቀርቧል።
ልኡል ወልዴ
መስከረም 28/2018 ዓ.ም
