በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለከተማ በአሰራር ክፍተቶች ምክንያት ተቋርጦ የነበረዉ የጤና መድህን እድሳት ዛሬ ይጀመራል ተብሏል

በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለከተማ የሚገኙ የጤና መድህን ተገልጋዮች የጤና መድህን እድሳት ጋር ተያይዞ ለጣቢያችን ቅሬታ አቅርበዋል።

የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ማንኛዉም የጤና መድህን አባል ከጥቅምት 1 ጀምሮ ባልታደሰ መታወቂያ በሆስፒታልም ሆነ በጤና ጣቢያ አገልግሎት እንዳይሰጥ ለክፍለከተሞች በደብዳቤ አሳዉቆ ነበር።

ይህንን ተከትሎ ክፍለከተሞች የአባላት መታወቂያን በወቅቱ በማደስ አገልግሎት እንዲሰጥ ያድርጉ ሲል በደብዳቤዉ አሳስቧል።

ለጣቢያችን ቅሬታ ያቀረቡ ተጠቃሚዎች በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለከተማ የጤና መድህን እድሳት በመዘግየቱ እና ባለመጀመሩ አገልግሎት ለማግኘት መቸገራቸዉን እንዲሁም ለተጨማሪ ወጪ ተዳርገናል ሲሉ ቅሬታቸዉን አቅርበዋል።

ከኢትዮ ኤፍ ኤም ጋር ቆይታ የነበራቸዉ በአቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን የቡድኖች አስተባባሪ አቶ ሀይለኢየሱስ አማረ ለቅሬታዉ ምላሽ ሰጥተዋል።

በክፍለከተማዉ በማህበረሰብ ጤና መድህን እድሳት ላይ የነበሩ አሰራር ክፍተት በመፈጠሩ የእድሳት ስራ አገልግሎት ተቋርጦ እንደነበር ተናግረዋል።

አቶ ሀይለኢየሱስ፤ የተፈጠረዉን የአሰራር ችግሮች ሲገልፁም ከዚህ ቀደም የነበረዉ የአከፋፈል ስርዓት በመቀየሩ እና ዘንድሮ እየተተገበረ ያለዉ የአከፋፈል ስርአት ፍትሀዊነት ለማስጠበቅ እንዲሆን መደረጉን አንስተዋል።

በመሆኑም በእያንዳንዱ ቤት መረጃ በመሰብሰብ መረጃዉ ትክክል ነዉ ÷አግባብ ነዉ የሚለዉን ከወረዳ አመራሮች ጋር በመለየት ለእያንዳንዱ አባወራ የኑሮ ሁኔታ አንፃር የአከፋፈል ስርአቱን የማስቀመጥ ሂደት ሲደረግ መቆየቱን ገልፀዋል።
በዚህ ሂደት ክፍተቶች መፈጠራቸዉን ያነሱት ሀላፊዉ ተሰብስቦ የተቀመጠዉ መረጃ እና የተሰጠዉ የአከፋፈል ስርአት ክፍተት ታይቶበታል መባሉን ተናግረዋል።

በመሆኑም ክፍተቶቹን ለማስተካከል ስለተሞከረ ከዛሬ ጀምሮ የጤና መድህን እድሳት ማድረግ እንደሚጀመር አቶ ሀይለኢየሱስ ገልፀዋል።

ቁምነገር አየለ

ጥቅምት 11/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *