በመንግስት የመዋቅር ለዉጥ ምክንያት እንዲከስሙ ወይም እንዲዋሀዱ የሚደረጉ ተቋማት ለኦዲት መስሪያ ቤቱ ስራ እንቅፋት መሆናቸዉን ጥናት ጠቁሟል።
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ከ2001 እስከ 2015 ዓ.ም በመንግስት የባለበጀት ተቋማት ላይ ያካሄዳቸው የተለያዩ ኦዲቶች በተቋማቱ የግልጸኝነትና ተጠያቂነት አሠራር እንዲሁም ሙስናንና ብልሹ አሠራርን በመከላከል ረገድ ያመጧቸውን ለውጦች ለመለየት ጥናት አስጠንቷል።
የጥናቱ ቡድን መሪ የሆኑት ዶ/ር ተመስገን ወርቁ እንደገለፁት፤ መንግስት ፖሊሲን ወይም ኘሮግራሞችን ለማስፈፀም በሚል ሚኒስትር መስሪያ ቤቶች ይሰነጠቃሉ ወይም ሊከስሙ ይችላሉ ብለዋል።
ሆኖም አንዳንድ መስሪያ ቤቶች ኦዲታቸዉ ሳያልቅ ከሌሎች ጋር ተዋህደዉ ይታያሉ ሲሉ ዶ/ር ተመስገን ይናገራሉ።
ይህ በመሆኑም ኦዲተር መስሪያ ቤቱ እየተቸገረ መገኘቱን እንዲሁም የሚፈልገዉን መረጃ ከማግኘቱም አንፃር ችግር መታየቱን ገልፀዋል።
የሚዋሀዱ ወይም እንዲከስሙ የሚደረጉ የመንግስት ተቋማት የፌደራሉን የኦዲት መስሪያ ቤት ስራ እየፈተኑት እንደሚገኝ ሰምተናል።
ከዚህ አንፃር መንግስት እንደዚህ አይነት ነገሮችን በሚያስብበት ጊዜ ቀደም ብሎ ይሄንን ተቋም በማግኘት የኦዲት ስራ ቀድሞ እንዲጠናቀቅ ማድረግ እንደሚገባ በጥናቱ አስቀምጠናል ብለዋል።
የኦዲት ግኝቶችን ተከትሎ ተገቢ ስልጣን ባላቸው አካላት መወሰድ የሚገባቸው ተጠያቂነትን የማረጋገጥ እርምጃዎች በሚፈለገው የቁርጠኝነት ደረጃ ላይ የሚገኙ ያለመሆናቸውን ጥናቱ ማሳየቱ ተገልጿል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ የኦዲት መስሪያ ቤቱ በመንግሥት በጀት ጥገኛ መሆኑ ÷ ለሰራተኞች ተመጣጣኝ ደሞዝ መክፈል አለመቻሉ ሀላፊነቱን እንዳይወጣ እንቅፋት ሆነዉበታል ተብሏል።
ይህ ጥናት በአዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲ የጥናትና ምርምር ባለሙያዎች ሳይንሳዊ ጥናት የተጠና መሆኑ ተነግሯል።
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ዋና ኦዲተር ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ፤ በጥናት ዉጤቱ የግምገማ መድረክ ባደረጉት ንግግር የኦዲት አሠራር ውጤታማነት በተግባር የሚገለጽ አስተዋጽኦ እስካላበረከቱ ድረስ ጥናቱ ለብቻው የሚፈለገውን ውጤት እንደማያስገኝ ተናግረዋል።
ቁምነገር አየለ
ጥቅምት 11/2018 ዓ.ም
