ድርጅቱ ሐሙስ ዕለት ይፋ ባደረገው ሪፖርቱ፤ ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ መንግስታት በጀታቸውን ለመሸፈን በአገር ውስጥ ባንኮች ላይ ጥገኝነታቸው እየጨመረ መምጣቱን አስታዉቋል።
ይህ ደግሞ ከአገር ውጭ ከሚበደሩት ብድር የበለጠ ከፍተኛ የወለድ ክፍያ እንዲከፍሉ የሚያደርጋቸው ሲሆን፤ በአገር ውስጥ አበዳሪዎች ላይ አዲስ ጫና እየፈጠረ መሆኑንም ገልጿል።
አይ ኤም ኤፍ እና የዓለም ባንክ በዋሽንግተን ባካሄዱት ዓመታዊ ስብሰባ ያወጡት የቅርብ ጊዜ የቀጣናዊ ኢኮኖሚ ትንበያ፤ የአገር ውስጥ የካፒታል ወጪ ከፍተኛ እንደሆነ አሳይቷል፡፡
በተጨማሪም የበርካታ የአገር ውስጥ የፋይናንስ ገበያዎች ያልዳበሩ እና የተከፋፈሉ በመሆናቸው ከፍተኛ የግብይት ወጪዎች እና የብድር ስርጭቶች እንዳሉ አስፍሯል።
አይ ኤም ኤፍ አክሎም በአሁኑ ወቅት በአንዳንድ አገሮች አዲስ የአገር ውስጥ ብድር ከውጭ ብድር በእጅጉ ውድ ሆኗል ያለ ሲሆን፤ መንግስታት በአገር ውስጥ ባንኮች ላይ ይበልጥ ጥገኛ በመሆናቸው የፋይናንስ ወጪዎች እየጨመሩ እና የግሉ ዘርፍ ኢንቨስትመንት እየቀነሰ መጥቷል ብሏል።
ሪፖርቱ የአገር ውስጥ ባንኮች የመንግስት ዕዳ ይዞታ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት ከቀሪዉ ዓለም በበለጠ በፍጥነት እያደገ መሆኑን አስታዉቋል፡፡
የአይ ኤም ኤፍ የአፍሪካ ዲፓርትመንት ዳይሬክተር አበበ አዕምሮ ስላሴ ለሮይተርስ እንደተናገሩት፤ ወደ አገር ውስጥ ፋይናንስ የሚደረገው ሽግግር መጨመር አገሮች በራሳቸው ገንዘብ ለመበደር ያላቸውን አቅም ቢያሳይም ከፍተኛ ስጋቶችንም የያዘ ነዉ፡፡
ዳይሬክተሩ፤አጠቃላይ የህዝብ ዕዳ ግማሽ ያህሉ በአገር ውስጥ ባንኮች የተያዘ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ባለፉት ዓመታት የውጭ ፋይናንስ ማግኘት ቀላል አልነበረም ያሉ ሲሆን፤ መንግስታት ዕዳቸውን ለመክፈል ከተቸገሩ ከመጠን ያለፈ የአገር ውስጥ ብድር በባንክ ዘርፉ ላይ ችግር ሊፈጥር ይችላል ሲሉ አስረድተዋል።
ለዓመታት በከፍተኛ የብድር ወጪዎች እና በኢኮኖሚያዊ አለመረጋጋት ምክንያት ከዓለም አቀፍ የካፒታል ገበያዎች ውጭ የቆዩ አንዳንድ የአፍሪካ አገሮች ከ2024 ጀምሮ ወደ ዓለም አቀፍ የቦንድ ገበያዎች በጥንቃቄ መመለስ ቢጀምሩም፤ ብዙዎች አሁንም ዕዳ ዉስጥ የመውደቅ ስጋት አለባቸው ሲል የዘገበዉ አፍሪካ ኒዉስ ነዉ።
እስከዳር ግርማ
ጥቅምት 11/2018 ዓ.ም
